መጋቢት 24 የሕዳሴ ግድብ ከውድቀት ያንሰራራበትና ወደ ታሪካዊ ምዕራፍ የተሸጋገረበት ነዉ – ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ

You are currently viewing መጋቢት 24 የሕዳሴ ግድብ ከውድቀት ያንሰራራበትና ወደ ታሪካዊ ምዕራፍ የተሸጋገረበት ነዉ – ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ

AMN – መጋቢት 24/2018 ዓ.ም

መጋቢት 24 የሕዳሴ ግድብ መሠረት የተጣለበት ብቻ ሳይሆን ከውድቀት እንዲያንሰራራ የተደረገበት እና ወደ ታሪካዊ ምዕራፍ የተሸጋገረበት ዕለት መሆኑን የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ገለጹ፡፡

ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ከኤ ኤም ኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ ፣ መጋቢት 24 መሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት የሕዳሴ ግድብ ፣መጀመሪያ ላይ በነቃ የህዝብ ተሳትፎ የዘመናት ቁጭትን ለመሻር ግንባታው ቢጀመርም በሂደት ፕሮጀክቱን ወደ ውድቀት የሚመሩ ችግሮች ውስጥ ተተብትቦ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ መጋቢት 24 የመጣው የለውጡ መንግሥት ለፕሮጀክቱ ከውድቀት መዳን ትልቅ እድል ያመጣ መሆኑን ነው የጠቀሱት፡፡

የለውጡ መንግሥት የሕዳሴ ግድብ አንሰራርቶ ከፍጻሜ እንዲደርስ ወሳኝ የማስተካከያ ርምጃዎችን መውሰዱን ኢንጂነር ክፍሌ ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ወደ አመራርነት እንደመጡ ግድቡን መጎብኘታቸውን ያስታወሱት ዋና ሥራ አስኪያጁ ፣ ጥናት ተደረጎ ችግሮቹን በመለየት ፕሮጀክቱን ለማዳን ርብርብ እንዲደረግ አስችለዋል ብለዋል፡፡

በተከናወነው የእርምት ርምጃ ፕሮጀክቱን ሊሠሩ የሚችሉ ኮንትራክተሮች እንዲረከቡትና ከቦርድ ጀምሮ የአመራር ማስተካከያ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከ12 ጊዜ በላይ ጉብኝት ማድረጋቸውን በመጠቅስ ለስኬቱ የርሳቸው ክትትል ሚናው የጎላ እንደነበር አንስተዋል፡፡

የታችኛው ተፋሰስ አንዳንድ ሃገራት የእጅ አዙር ጦርነት ፣ ኮቪድ እና የሰሜኑ ጦርነት የመሳሰሉ ታግዳሮቶች ቢኖሩም ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ፕሮጀክቱን አጠናቆ ከፍጻሜ ማድረስ ትልቁ ጦርነት ነው ” በሚል በያዙት ቆራጥ አቋም ለስኬት መብቃቱን ተናግረዋል፡፡

የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ለመፈጸም አርአያና ትምህርት የሰጠ መሆኑን ነው የግድቡ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ የገለጹት፡፡

የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ፣ ሕዝብና መንግሥት አንድ ሆነው ከሰሩ ሁሉንም ፈተና በማለፍ ከፍጻሜ ማድረስ እንደሚቻል ፣አንድነት ሐገርን እንደሚለውጥ ትምሕርት የሠጠ ነው ብለዋል፡፡

ፕሮጀክቶች በአግባቡ ከተመሩና ክትትል ካለ የውጭ ርዳታ ሳይጠበቅ ፣ የሐገርን ሐብት በማሰባሰብ ትልልቅ ሥራዎችን መፈጸም እንደሚቻል የህዳሴ ግድብ አብነት መሆኑን ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ገልጸዋል፡፡

በታደሠ ሽፈራው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review