AMN መጋቢት 24/2018
ኢትዮጵያ እና ቻይና የንግድና የፋይናንስ ትብብራቸውን ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር እንደሚሰሩ አስታወቁ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ከቻይና ሕዝባዊ ባንክ ገዢ ፓን ጎንግሼንግ ጋር በቤጂንግ ተወያይተዋል። ውይይቱ የንግድ እና የኢንቨስትመንት ትስስርን ይበልጥ ለማሳደግ ያለመ ነው።
በውይይቱ ወቅት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቡድን 20 (G20) የጋራ ማዕቀፍ ስር ስላለው የኢትዮጵያ የዕዳ ሽግሽግ ሂደት አጠቃላይ ወቅታዊ መረጃ ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያን ጠንካራ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) ዕድገት እንዲሁም የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር እና የውጭ ምንዛሪ ክምችትን መልሶ ለመገንባት የተከናወኑ ስኬታማ ጥረቶች ተነስተዋል።
የንግድ ልውውጥ ሂደቱን ይበልጥ ቀልጣፋ ለማድረግ እንዲቻል፣ የሁለትዮሽ የገንዘብ ልውውጥ መስመሮችን (Swap lines) ለመዘርጋትና ለንግድ ሥራዎች የሚውሉ የፋይናንስ አማራጮችን ለማስፋት በሁለቱም ወገኖች በኩል ስምምነት ላይ ተደርሷል።
የብሔራዊ ባንክን የውጭ ምንዛሬ ክምችት ለማጠናከር የቻይናን ገንዘብ (RMB) የመጠቀም አስፈላጊነትን ያነሱት እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ለዚህም እንደ አየር መንገድ ካሉ ተቋማት የሚገኘውን ገቢ መጠቀምና የንግድ ክፍያዎችን ወደ ቻይና ገንዘብ መቀየር እንደ መፍትሔ አስቀምጠዋል።
ይህ ስትራቴጂያዊ እርምጃ የቻይና ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ያላቸውን የሥራ እንቅስቃሴ ከማቀላጠፉም በላይ፣ አዳዲስ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ እንደ ትልቅ ማበረታቻ እንደሚያገለግል አመልክተዋል።
ገዢዎቹ በተጨማሪም የብሔራዊ የክፍያ ሥርዓት መሠረተ-ልማቶችን በማቀናጀት ድንበር ተሻጋሪ ግብይቶችን ዘመናዊ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይም መክረዋል።
የቻይና ሕዝባዊ ባንክ ገዢ ፓን ጎንግሼንግ ፓን ጎንግሼንግ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት በድንበር ተሻጋሪ የባንኮች የክፍያ ሥርዓት (CIPS) ውስጥ ሊቀላቀሉ የሚችሉባቸውን መንገዶች እና የችርቻሮና የንግድ ክፍያዎችን ለማቀላጠፍ የቻይና ዩኒየን ፔይ (UnionPay) አገልግሎትን ማስፋፋት ስለሚቻልበት ሁኔታ አብራርተዋል።

በተጨማሪም፣ሁለቱም ወገኖች በማዕከላዊ ባንክ ዲጂታል ገንዘብ (CBDC) ልማት ዙሪያ የተወያዩ ሲሆን፣ የቻይና ሕዝባዊ ባንክ የኢትዮጵያን የዲጂታል ፋይናንስ ዕድገት ለማፋጠን የአቅም ግንባታ እና የልምድ ልውውጥ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል።
የባንኩ ገዢ ኢትዮጵያ በቅርቡ ያከናወነቻቸውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች እና የዕዳ ዘላቂነትን ለማረጋገጥ የወሰደችውን እርምጃ አድንቀዋል።
ሁለቱም ከዓለም አቀፍ የንግድ ልውውጥ እና ከዲጂታል ፋይናንስ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ጋር የሚጣጣም የረጅም ጊዜ እና የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ አጋርነት ለመቀጠል ያላቸውን ቁርጠኝነት በድጋሚ ማረጋገጣቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር ለኤኤምኤን በላከው መረጃ አመልክቷል።