አምባሳደር ቆንጂት ስነጊዮርጊስ የአፍሪካ ዲፕሎማሲ እሴቶች ተምሳሌት ነበሩ

You are currently viewing አምባሳደር ቆንጂት ስነጊዮርጊስ የአፍሪካ ዲፕሎማሲ እሴቶች ተምሳሌት ነበሩ

AMN መጋቢት 29/2018

የአፍሪካ ዲፕሎማሲ ከፍተኛ እሴት በተግባር ያሳዩ ታላቅ ዲፕሎማት ነበሩ ሲሉ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ ገለጹ።

ሊቀመንበሩ በኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ታሪክ ውስጥ ስመጥር በሆኑት አምባሳደር ቆንጂት ስነጊዮርጊስ ህልፈት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልጸዋል።

ሊቀመንበሩ አምባሳደሯን የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት አገልግሎት ፈር ቀዳጅ፣ ታላቅ ዲፕሎማት እና ህይወታቸውን ለሀገራቸውና ለአህጉሪቱ እድገት የሰጡ ጽኑ አፍሪካዊት ሲሉ አወድሰዋቸዋል።

አምባሳደር ቆንጂት ስነጊዮርጊስ ለበርካታ አስርተ አመታት የዘለቀ አርአያነት ያለው ሙያዊ ስኬት ማስመዘገባቸውንና ከኢትዮጵያ ቀዳሚ ሴት አምባሳደሮች አንዷ በመሆንም ለአፍሪካውያን ሴት ዲፕሎማቶች የብርሃን ፋና መሆናቸውን አመልክተዋል።

የአፍሪካን ጥቅም ለማስከበርና ዓለም አቀፍ ትብብርን ለማጠናከር የነበራቸው የማይናወጥ ቁርጠኝነት ለአህጉራዊ የጋራ ግቦች መሳካት የጎላ ሚና እንደነበረውም አውስተዋል።

ሊቀመንበሩ አምባሳደር ቆንጂት በታማኝነት፣ በልዩ ብቃት እና ለጋራ የወደፊት እጣ ፈንታችን የነበራቸው ጽኑ ቁርጠኝነት የአፍሪካ ዲፕሎማሲ እሴቶች ያላቸውን ጽኑ አቋም ያሳየ መሆኑንም ነው ያነሱት።

የአምባሰደሯ የዲፕሎማሲ አሻራ ለቀጣይ ትውልድ ዲፕሎማቶች፣በተለይም ለሴቶች፣በድፍረትና በዓላማ እንዲያገለግሉ ዘላቂ መነሳሳት ሆኖ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

ሊቀመንበሩ በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ስም ለአምባሳደር ቆንጂት ቤተሰቦች፣ ለኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ፣ እንዲሁም ለሁሉም አፍሪካውያን ልባዊ መጽናናትን ተመኝተዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review