AMN መጋቢት 29/2018
የኢትዮጵያ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አዲስ የልማት ምዕራፍ መክፍቱን የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ ገዢ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ገለጹ።
የገንዘብ ሚኒስቴር ባለፉት 18 ወራት የተከናወኑ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ እና መዋቅራዊ ማሻሻያዎችን ውጤታማነት የሚገመግም ዝርዝር ሪፖርት ይፋ አድርጓል።
በሪፖርቱ መሠረት የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የተወሰዱ እርምጃዎች ውጤት እያሳዩ መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን የወጪ ንግድ ገቢ በማሳደግ ረገድ እንዲሁም በሌሎችም ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ተመዝግበዋል።
የብሔራዊ ባንክ ገዢ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ ማሻሻያው በኢትዮጵያ አዲስ የልማት ምዕራፍ የከፈተና ተጨባጭ ውጤቶች እየተመዘገቡበት መሆኑን ገልጸዋል።
ሪፖርቱ በኢኮኖሚ ማኔጅመንት ቡድን አማካኝነት በራስ አቅም የተዘጋጀ መሆኑ በአሁኑ ወቅት በተቋማት ውስጥ ጠንካራ አቅም ያላቸው ባለሙያዎች እየተፈጠሩ መሆኑን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት የመንግሥት ተቋማት የፖሊሲ ነጻነት ያላቸው መሆኑ ለማሻሻያው ስኬታማነት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ጠቁመዋል።

ብሔራዊ ባንክ ትልቅ እመርታ እና የፋይናንስ ሥርዓቱን ጤናማነት ለማረጋገጥ አመርቂ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ ባንኩ የዋጋ ማረጋጋት እና የፋይናንሻል ዘርፉን ጤነኛነት ለመጠበቅ በርካታ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ የተደረገው ሪፖርቱ እስካሁን የተመዘገቡ ስኬቶችን ብቻ ሳይሆን፣ በቀጣይ የሚከናወኑ ተግባራትንም በዝርዝር ማካተቱን ጠቅሰዋል።
የአምራች ሴክተሩ እንዲነቃቃ እና ለሀገር ኢኮኖሚ የሚጠበቀውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የሀገር በቀል ሪፎርሙ ውጤት እያስገኘ መሆኑን ገልፀው፥ ሪፖርቱ የኢትዮጵያን ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትክክለኛ አቅጣጫ የሚያሳይ መሆኑን ማረጋገጣቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡