AMN ሚያዚያ 01/ 2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ለአፍሪካ ኩራት መሆኑን የብሩንዲ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንትና የአፍሪካ ህብረት የወቅቱ ሊቀመንበር ኤቫሪስት ንዳይሽሚዬ ገለጹ፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ይፋዊ ግብዣ ለሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ የሚገኙት የብሩንዲ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንትና የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሰብሳቢ ኤቫሪስት ንዳይሽሚዬ፤ በኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር ጉብኝት አድርገዋል።
ፕሬዝዳንቱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሲደርሱ የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ከከፍተኛ ጄኔራል መኮንኖች ጋር በመሆን ደማቅ ወታደራዊ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ፕሬዝዳንት ኤቫሪስት ኢንዳይሽሚዬ ከሚኒስትሯ ጋር በነበራቸው የሁለትዮሽ ውይይት፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ወታደራዊ ትብብር ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ሰፊ ምክክር አድርገዋል።
በውይይቱም ፕሬዝዳንቱ፤ ብሩንዲ የሰላም ዕጦት ውስጥ በነበረችበት ወቅት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ሰላም በማስከበር ረገድ ላበረከተው ሚናና ለከፈለው መስዋዕትነት የላቀ ምስጋና አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሀገሩን ሉዓላዊነት ከማስጠበቅ ባለፈ ለአፍሪካ ኩራት የሆነ ሰራዊት መሆኑንም በማንሳት አድናቆታቸውን ገልፀዋል።
የሁለቱ ሀገራት መከላከያ ሰራዊት አባላት በሶማሊያ ሰላም የማስከበር ተልዕኮ ላይ በጋራ ውጤታማ ተግባራትን ማከናወናቸውን አስታውሰው፤ ኢትዮጵያ ለብሩንዲ ሰራዊት በስልጠና እና በተለያዩ ድጋፎች ስታደርግ የቆየችውን አስተዋፅኦ አድንቀዋል።

በርካታ የብሩንዲ ሰራዊት አባላትም በኢትዮጵያ ስልጠና በመውሰድና አቅማቸውን በመገንባት ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን በመጥቀስ፤ አሁንም የብሩንዲ መከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያን ድጋፍና ልምድ እንደሚፈልግ ተናግረዋል።
ይህ ጉብኝት በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ወታደራዊ ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግረው ፕሬዝዳንቱ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።
የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ በበኩላቸው፤ የፕሬዝዳንቱ ጉብኝት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ጥብቅ አጋርነት የሚያሳይ ጉልህ ምልክት መሆኑን ገልፀው፤ ጉብኝቱ ትብብሩን ይበልጥ ለማጠናከርና ሙያዊ ልምዶችን ለመለዋወጥ ወሳኝ አጋጣሚ መሆኑን አስታውቀዋል።
በተለይም በሁለቱ አገራት የመከላከያ ተቋማት መካከል ያለውን ወታደራዊ ትብብር ይበልጥ ለማሳደግ፣ በወታደራዊ ኢንዱስትሪ መስኮችና በጋራ ወታደራዊ ስልጠናዎች ላይ በትኩረት ለመስራት ዝግጁ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሯ ይህ ትብብር የሁለቱን ሀገራት የጋራ ደህንነት ከማረጋገጥ ባለፈ ለቀጠናዊ ሰላም መጠበቅ ያለውን አህጉራዊ ኃላፊነት በጋራ ለመወጣት የሚያስችል ወሳኝ እርምጃ ነው ሲሉ መግለጻቸዉን የመከላከያ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡