የፓርቲዎቹ የምርጫ ቅስቀሳ ሲቃኝ

You are currently viewing የፓርቲዎቹ የምርጫ ቅስቀሳ ሲቃኝ

ወጣት ኤቢሳ ኪዳኔ የጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ነዋሪ ነው፡፡ ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለጸው፣ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በቀጣይ ‘ለራሴና ለሀገሬ ይጠቅማል’፤ ‘የተሻለ ይሰራልኛል’ የሚለውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ የምርጫ ካርድ አውጥቷል፡፡ በመገናኛ ብዙሃን የሚተላለፉ የምርጫ ክርክሮችንም እየተከታተለ ይገኛል። የፖለቲካ ፓርቲዎች ያላቸውን ፕሮግራምና ፖሊሲ ለህዝብ በግልጽ እያቀረቡና እያስተዋወቁ ነው፡፡ ይህም የትኛው ፓርቲ የህዝብን ህይወት የሚያሻሽል፣ ሀገርን የሚያሻግር ሀሳብ ይዞ እንደመጣ ግንዛቤ ይፈጥራል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሞላ ጎደል ስርዓት ባለው መልኩ፣ በመከባበር፣ በመደማመጥ፣ ሀሳብ ላይ ትኩረት በማድረግ በተለያዩ ጉዳዮች ክርክር ሲያደርጉ መታዘቡን የሚናገረው ወጣት ኤቢሳ፣ በምርጫ ቅስቀሳና የምረጡኝ ዘመቻ ወቅትም በዋናነት ሀገርን ከድህነት ለማውጣት ያስችላል የሚሉትን ሀሳብ ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው አንስቷል፡፡

ሌላኛው በአዲስ ከተማ ወረዳ 14 የሚሰሩትና በሸገር ከተማ አስተዳደር ቡራዩ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ጌታሁን ቀንዓ በምርጫ መሳተፍ የዜግነት መብት እንደመሆኑ ‘ለሀገርና ወገን የተሻለ ይሰራል’ ብለው ለሚያስቡት የፖለቲካ ፓርቲ ድምፅ ለመስጠት የምርጫ ካርድ አውጥተዋል፡፡  በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የፖለቲካ ፓርቲዎች በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ሀሳብ እያስተዋወቁና እየተከራከሩ ነው፡፡ ይህም በቀጣይ በተሻለ መልኩ ሀገርን የሚመራ ፓርቲ መምረጥ እንድንችል ይረዳናል። ገዥው ፓርቲ ባለፉት ዓመታት ባከናወናቸው ስራዎች የመጡ ውጤችንና በቀጣይ ሊሰራ ያቀዳቸውን ስራዎች፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም የያዙትን ፖሊሲና ፕሮግራም እያቀረቡ ይገኛሉ ሲሉ ምልከታቸውን ተናግረዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች አለን የሚሉትን ፖሊሲና ፕሮግራማቸውን በዴሞክራሲያዊ መንገድ እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡ አልፎ አልፎ አንዳንድ ተከራካሪዎች ወጣ ያሉና ሌሎችን የሚያስቆጣ ሀሳብ ሲያቀርቡ ክርክሩን ለህዝብ ተደራሽ እንዲሆን እያደረጉ ባሉ የሚዲያ ሰዎች (ጋዜጠኞች) እንዲያስተካክሉና እንዲታረሙ አስተያየት እየተሰጣቸው ክርክሩ በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ እንደሚገኝ አቶ ጌታሁን ትዝብታቸውን አጋርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለማከናወን የጊዜ ሰሌዳ ይፋ አድርጎ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሆነ ይታወቃል። በቅድመ ምርጫው ሂደት የመራጮች ምዝገባ በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት ፓርቲዎች የምርጫ ማኒፌስቷቸውንና ፕሮግራማቸውን እያስተዋወቁ ይገኛሉ፡፡ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክን ጨምሮ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃንም ተፎካካሪ ፓርቲዎች በተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ ክርክርና የምረጡኝ ቅስቀሳ እያደረጉ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድና የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የፖለቲካ ፓርቲዎች በመገናኛ ብዙሃን ፕሮግራማቸውንና ፖሊሲዎቻቸውን እንዲያስተዋውቁ፣ የግል ዕጩዎችም አማራጭ ሀሳባቸውን እንዲያጋሩና የምርጫ ቅስቀሳ እንዲያደርጉ፣ ከመራጩ ጋር እንዲተዋወቁ  ነጻ የአየር ሰዓት ድልድል ተደርጓል፡፡ በዚህም መሰረት በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥንና ጋዜጣ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅስቀሳ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

ለመሆኑ የፖርቲዎች የምርጫ ክርክርና ቅስቀሳ ምን ላይ ቢያተኩር ለሀገርና ህዝብ የሚጠቅም ይሆናል? ከዚህ አንጻርስ ምን ዓይነት ጥንካሬና ክፍተቶች እየታዩ ነው? በቀጣይስ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምን ይጠበቅባቸዋል?

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነፃ፣ ፍትሀዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በሁሉም የምርጫው ምዕራፍ የባለድርሻ አካላት ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ በምርጫ ክርክሮችና ቅስቀሳ ወቅትም የፖለቲካ ፓርቲዎች በኃላፊነት ስሜት መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል። በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር ዐዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 44 ንኡስ አንቀፅ 3 ስለምርጫ ዘመቻ እንደተብራራው፤ አንድ እጩ ተወዳዳሪ በእጩነት ተመዝግቦ የመታወቂያ ካርድ ካገኘበት ቀን አንስቶ ምርጫው አራት ቀን እስኪቀረው ድረስ ከአስተዳደሩም ሆነ ከማዘጋጃ ቤት ፈቃድ መጠየቅ ሳያስፈልገው፤ በጽሑፍ በማሳወቅ ብቻ እና ሕጋዊ ግዴታዎቹን በማክበር በራሱም ሆነ በደጋፊዎቹ አማካኝነት የድጋፍ ስብሰባዎችን የመጥራት ወይም ሰላማዊ ሰልፍ የማደራጀት መብት አለው፡፡ እንዲሁም ለምርጫ ውድድሩ ይጠቅሙኛል ያላቸውን መረጃዎች ከቦርዱ የማግኘት መብት ይኖረዋል። የምርጫ ውድድር እንቅስቃሴ ህገ መንግሥቱና አግባብነት ያላቸውን ሌሎች ህጎች፣ የመራጮችን መብት፣ የሌሎች እጩዎችን የመወዳደር መብት በማክበር በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ መካሄድ አለበት፡፡

በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና አለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ሙሉዓለም ኃ/ማርያም ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት፣ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ክርክርና ስነ ምግባር ወቅት ምን ማድረግ እንዳለባቸውና እንደሌለባቸው የሚገልፅ በጋራ የተስማሙበት የስነ ምግባር ደንብ አለ፡፡ ከዚህ አኳያ ደንቡን አክብረው መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ክርክርና ቅስቀሳ ሲያደርጉ መከባበርን መሰረት ባደረገ መልኩ መሆን አለበት፡፡ ሀሳብን በሀሳብ መሞገት፣ በተረጋገጠ መረጃ መተቸት፣ ከስም ማጥፋትና ጥላቻ ንግግር መቆጠብ ይገባቸዋል፡፡ ሀሳቡን ትቶ ሰውዬውን ከመሞገት (Againest the person fallacy) መውጣት ያስፈልጋል፡፡ የትኛውም ፓርቲ የሚያቀርበውን ሀሳብ ማጣጣል የሚቻለው በሀሳብ ነው፡፡

ዓለም አቀፍ የግልግል እና እርቅ ባለሙያው ሕዝቅያስ አሰፋ (ፕ/ር) እንደሚሉት፣ የብዙ ፓርቲ ዘመቻዎችና ምርጫዎች የህብረተሰቡን ስሜት በመነካካት ያለፉ ቅሬታዎች፣ አለመጣጣሞች፣ ፍርሃትና ጥርጣሬዎች እንዲያገረሹ እንዳያደርጉ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ሙሉዓለም እንደሚናገሩት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምረጡኝ ቅስቀሳ ወቅት በፖሊሲዎችና ፕሮግራሞች፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ላሉ ችግሮች ተግባራዊ መፍትሔዎች ላይ ያተኮረ ሀሳብ ማቅረብ ይኖርባቸዋል። እስከአሁን ባለው ሂደትም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰላማዊ መንገድን መርጠውና ዝግጁ ሆነው በምርጫ ሂዳት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በቴሌብዥን መስኮት በመከራከር እያሳዩ ያለው ተሳትፎ፣ ዝግጁነትና ቁርጠኝነት የሚደገፍና በበጎ ጎን የሚታይ ነው፡፡ በአብዛኛው የፖሊሲ አማራጮችና ዋና ዋና የሀገሪቱ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ሀሳባቸውን እያቀረቡ ይገኛሉ። መገናኛ ብዙሃንም ተነሳሽነት ወስደው የምርጫ ክርክሮች መድረክ በማመቻቸት የፖለቲካ ፓርቲዎች በሰፊው የፖሊሲ አማራጮች እንዲያቀርቡ እየሠሩ በመሆኑ የሚበረታታና በጎ እርምጃ ነው፡፡

በሌላ በኩል “ሁሉም ፓርቲዎች ባይሆኑም አንዳንዶቹ የራሳቸውን ሀሳብ፣ ፖሊሲና ፕሮግራም ማስተዋወቅ ላይ ከማተኮር ይልቅ ግለሰብ ላይ ያነጣጠረ፣ የመወነጃጀልና የመጠቃቃት ዓይነት (against the person fallacy) የሚመስል ነገር ተመልክተናል” የሚሉት የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ሙሉዓለም፣ ጥልቀት ያለው የፖሊሲ አማራጭ ሀሳቦችን በማቅረብ ረገድም ክፍተት ይታያል፡፡ አንዳንዶች ህዝቡ ሊረዳው በሚችል መልኩ በግልፅ ቋንቋ የተቀመጠ ፖሊሲና ስትራቴጂ አላቸው ብሎ በድፍረት ለመናገር ያስቸግራል። ይዘውት የመጡት ፖሊሲም በትክክል ምን እንደሆነ አይታወቅም፡፡ ተግባራዊ መፍትሔ ከማቅረብ አኳያም ውስንነቶች ይታያሉ፡፡ ከዚህ አኳያ በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች ያላቸውን ፖሊሲና ፕሮግራም ግልፅ በሆነ ቋንቋ ለህዝቡ ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው ያስረዳሉ፡፡

የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ሙሉዓለም እንደሚናገሩት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክር ሲያደርጉ ከጥላቻና እርስ በእርስ መጠቃቃት የፀዳ መሆን ይኖርበታል። የምርጫ ቅስቀሳ በፓርቲዎች፣ በተከራካሪዎች መካከል መከባበር፣ የዴሞክራሲ ባህል ለማሳደግ፣ ግልጽ የሆነ የፖሊሲና ስትራቴጂ አማራጭ ለማስቀመጥ ይጠቅማል፡፡ ለመራጩ ህዝቡ ደግሞ ‘ማንን መምረጥ አለብኝ’ የሚለውን ለመወሰን እድል ይፈጥራል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ማንሳት ያለባቸው ሀገራዊ ጉዳዮች በተመለከተ የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ሙሉዓለም ኃ/ማርያም እንደሚሉት፤ “የሀገሪቱ አንገብጋቢና ትላልቅ የሚባሉ ችግሮች ላይ ትኩረት ማድረግ፣ መውጫ መንገዱን ማንሳትና ማመላከት ይኖርባቸዋል፡፡ ለምሳሌ፡- የሀገር ሰላምና ደህንነት ቁልፍ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎች ዘላቂነት ያለው ሰላምና የተረጋጋ ሀገር ለመፍጠር ምን መስራት ያስፈልጋል? በምን መንገድ ነው የተረጋጋና ጠንካራ ሀገር መፍጠር የሚቻለው ላይ ትኩረት ማድረግ አለባቸው፡፡ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ማለትም የዋጋ ግሽበት፣ የወጣቶችና ሴቶች ስራ አጥነትና መሰል ጉዳዮች ላይ አማራጭ ሀሳቦችን ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ ፍትህና የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ የመንግስት አወቃቀርና የፌዴራል ስርዓት አንገብጋቢ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል ናቸው” ብለዋል፡፡

በቀጣይ በሚኖረው የምርጫ ቅስቀሳ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሥነ ምግባርን አክብረው መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል። አባሎቻቸውና ደጋፊዎቻቸው በምርጫው ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ፣ ህግና ስርዓትን አክብረው እንዲንቀሳቀሱ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ ላይ መስራት ያስፈልጋል፡፡  ምርጫውን የሚያስፈፅመው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድና ሌሎች የምርጫ ተቋማት በገለልተኝነት መስራት፣ መገናኛ ብዙሃንም ለምርጫ ቅስቀሳ የሚሰጡት የአየር ሰዓትና አምድም ፍትሀዊነት እንዲሆን ማድረግ ለምርጫው ስኬታማነት ወሳኝ እንደሆነ የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ሙሉዓለም ያስረዳሉ፡፡

በጥቅሉ የምርጫ ቅስቀሳ ወይም የምረጡኝ ዘመቻዎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀሳባቸውን፣ የፖሊሲና ፕሮግራም አማራጮቻቸውን ለመራጩ ህዝብ ለመሸጥና መራጩም ህዝብ የተወዳዳሪዎችን ማንነት አውቆ መምረጥ እንዲችል ያግዛል፡፡ ከዚህ አኳያ የፖለቲካ ፓርቲዎች መራጩን ለማሳመን በሚያደርጉት ጥረት ከጥላቻ፣ የተፎካካሪን ስብእና ከማቃለልና ማጥላላት፣ ከሀሰተኛ መረጃ መራቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review