ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ኅብረት ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ግንኙነት ማጠናከር ትሻለች

AMN – ታኅሣሥ -8/2017 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ኅብረት ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ግንኙነት ማጠናከር እንደምትሻ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) አስታወቁ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ዛሬ በአዲስ አበባ መካሄድ በጀመረው የኢትዮጵያና የአውሮፓ ኅብረት የስትራቴጂክ አጋርነት መድረክ ላይ ነው።

በመድረኩ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) የሚመራ የኢትዮጵያ ልዑክ እና በአዲስ አበባ የሚገኙ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት አምባሳደሮች እና ተወካዮች እየተሳተፉ ናቸው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በዚሁ ጊዜ የአውሮፓ ኅብረት የኢትዮጵያ ቁልፍ የሠላምና የልማት አጋር መሆኑን ገልጸዋል።

አጋርነቱን ተጠቅማ ኢትዮጵያ ከኅብረቱ ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር እንደምትሻ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ከአውሮፖ ኅብረት አምባሳደሮችና ተወካዮች ጋር የሚደረገው ውይይትም በሠላምና ጸጥታ፣ በኢኮኖሚ ልማትና በባለብዙ ወገን ትብብር ላይ ያተኮረ መሆኑን ማመልከታቸውን ኢዜአ ዘግቧል ።

በኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት አምባሳደር ሶፊ ፍሮም ኢመስበርገር በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሠላምና መረጋጋት ወሳኝ ሚና እንዳላት አስረድተዋል።

የአውሮፓ ኅብረት በቀጣናው ሠላምና ደህንነት እንዲሰፍን የበኩልን ድርሻ እንዳለውም መናገራቸውን ውይይቱን የተከታተሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያና የአውሮፓ ኅብረት ያላቸውን ትስስር ለማጠናከር እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ2016 የስትራቴጂክ አጋርነት ትብብር መፈራረማቸው ይታወቃል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review