የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልእክት ማህበራዊ ጠንቆችን ከማህበራዊ አንቂዎች እንለይ ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በሀሳብ ድርቀት ክፉኛ የተመቱ፣ ቂም ጥላቻና ስር የሰደደ የሰብዕና ዝቅጠት የተጣባቸው ድኩማን የማህበራዊ ሚዲያ ጠንቆች ከየጎሬው የሚያሰባስበቸው ጉዳይ ቢኖር በደም ነጋዴነት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ቁማርና ርካሽ ሆድ ተኮር ትርፍ ብቻ ነው።
ባደገው ዓለም የማህበራዊ ሚዲያ አንቂ የሚባሉት ቀድመው የነቁና ነቅተው የሚያነቁ (enlightened የሆኑ)፣ የዕለት ሳይሆን የመጪው ትውልድ ሰብዕናና ግንባታ ጉዳይ የሚያሳስባቸው፣ በየሙያ ዲሲፕሊናቸው ዓላማ ተኮር ሆነው በተመረጠ መስክ ላይ ህብረተሰብን ማንቃትና ማሰለፍን ዒላማ አድርገው የሚንቀሳቀሱ ናቸው ብለዋል፡፡
የሀገራቸውና ህዝባቸው ሰላም፣ ነገና መጪው ዘመን አሳስቧቸው ቀን ከሌት የሚባትሉና የሚደክሙ ሁልጊዜም ምስጋና የሚቸራቸው የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች የሆኑ ማህበረሰብ አንቂዎች እንዳሉን ሁሉ፣ ለማህበራዊ አንቂነት ምዘና የማይበቁ፣ መሽቶ እስኪነጋ በክፋት የተፀነሰ ሀሳብ፣ በደም የሚሸጥ ድርሰት፣ የሚፅፉና የሚያሰራጩም አሉን። እንደነዚህ አይነቶቹ የሀሳብ ድሆች፣ ግለሰብ ሆነው የሀገር ያህል ከፍ እንዳሉት ምርጥ ማህበራዊ አንቂዎቻችን ሳይሆን በማህበራዊ ጠንቅነት ሊገለፁና ሊወገዙ የሚገባቸው የትውልድ ሰንኮፎች ናቸው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የሀሳብ ድሆቹ ማህበራዊ አንቂነትን ለማህበረሰባዊ ለውጥና ትውልድ ግንባታ ሳይሆን ለሁከትና ብጥብጥ፣ ጥቃትን፣ ቁርሾና መጠፋፋትን ኑሮ አድርገው በመላላክ ሱሰኝነት የጥቂት ጨለምተኞችን እኩይ የፖለቲካ ፍላጎት ለማሟላት ይጠቀሙበታል። የሚከውኑት ጥፋትና ድራማ ወዴት እንደሚወስዳቸው የማያውቁና መዳረሻቸውም በጨለማ የተሞላ ነው።
ግባቸው ሆድና ኪሳቸውን መሙላትን ብቻ ነው። ከርስና ኪሳቸው እስኪሞላ ድረስ ለወለዷቸው ልጆች የነገ እጣ ፈንታ ጭምር ሳያስቡ የሚባክኑ የሃሳብ ረሃብተኞች ናቸው። የማህበረሰብ ጉዳቶች፣ የቤተሰብ መበተን፣ የሀገር መበጥበጥ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ለእነሱ ትርጉም አልባ ነው።
በተናጠልም ሆነ በስብስብ ዋናው ትኩረታቸው ትርፍ እስካስገኘ ድረስ የፖለቲካ ንግድ ማካሄድና ለሚላላኩት አካል ጠጠር ሆኖ ማገልገል ነው። የፖለቲካ ንግድ ያለ ግጭት ትርፍ የለውምና ያለ ሀሰተኛ መረጃ አይንቀሳቀሱም፤ ጭር ሲል አይወዱም።
ሰላም፣ እድገት ብልፅግና ይሉት ሃሳብና ተግባር ሆዳቸውን ባርባር ያስብለዋል። የግጭት ርሃብ ሱስና ጥማታቸው የሚሞላው በደም ማፍሰስና ጥላቻን እለት ተዕለት በማዋለድ ነው።
ስለሆነም የባህል ወይም የህግ ውክልና ሳይኖራቸው ራሳቸውን የአንድ አካባቢ፣ ጎሳ ወይም ማህበረሰብ ወኪልና ጠበቃ አድርገው ለመታየት ስስ የሆኑ ስሜትን የሚኮረኩሩ ጉዳዮችን እየነቀሱ፣ የሀሰት ማንነት ጭምብል ለብሰው በስሙ የሚነግዱበትን አካል ጭምር ትርፍ እስካስገኘላቸው ድረስ ጭዳ አድርገው፣ አዋርደው፣ አሰቃይተውና ዘግናኝ ግድያ ፈፅመው ያለምንም ሀፍረት በክህደታቸው እየኮሩ ግለ ሰብዕናቸውን ለማላቅ የሚንቀሳቀሱ ናቸው።
እንደዚህ አይነቶቹ አካላት ሲያሻቸው በአንድ ወቅት መዘባበቻ ሲያደርጉት ለነበረው አካል ዋና ጠበቃ ሆነው ብቅ ይላሉ። በእኩይ ድርጊታቸው ለፈሰሰው ደም፣ ለጠፋው ህይወት ፀፀት የለንም እያሉ፣ በቀጣይ ለሚያስቡትና ለሚያልሙት ሴራ ማንጠልጠያ ይሆነናል ብለው በገመቱ በማንኛውም ጊዜ አዳዲስ ድርሰቶችን ፅፈው፣ ተዋናይ አዘጋጅተው ትንታኔ እየሰጡ “ጅብ የማያውቁት አገር ሄዶ ቁርበት አንጥፉልኝ አለ” እንደሚባለው አዛኝ መስለው፣ ልባቸው እንደተሰበረ ሆነው ይቀርባሉ፤ የአዞ እምባም ያነባሉ።
በመንደራቸው ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ እንዳይሄዱ ሲታገዱ፣ ሄደው የተገኙም ሲገደሉ፣ መምህራንና የጤና ባለሙያዎች በጠራራ ፀሐይ በእነዚህ ጨካኞችና እነሱ በሚያሰማሯቸው ደናቁርት ህይወታቸው ሲቀጠፍ ትንፍሽ ሳይሉ፣ ይህን ለማስቆም የሚሰሩ እጆችን ሊያነውሩ ይሞክራሉ፤ በሀሰት ይከሳሉ፤ በስሜት ህዝብን እርስ በእርስ ለማጣላትና ለማባለት ይቆምራሉ። ህዝብ ለእነሱ የንግድ ምልክት እንጂ ምናቸውም አይደለም። እንዲያውም የንፁሃንን ሞት በጭፋራ ያጅባሉ። ገዳይን ጀግናችን እያሉ ያሞካሻሉ።
ትርፍ የሚያገኙት ከፖለቲካ ንግድ ስለሆነ ነውር የሚባል ነገር በደጃቸው የለም። ለእነሱ አማራነት፣ ኦሮሞነት፣ ትግራዋይነት ወዘተ የስም መቆመሪያና የጥፋት ማወራረጃ እንጂ የሰብዓዊ ክብርና ማንነት መለኪያ አይደለም።
በሠፈራቸው በጽንፈኝነት እና በአረመኔያዊ ግድያ በኢሰብአዊ መንገድ ስለሚሞቱ ህፃናት፣ ወጣቶች፣ ሙያተኞች፣ አርሶአደሮች ትንፍሽ አይሉም። የዚህ ዋነኛ አመክንዮ ደግሞ የገዳይና አረመኔያዊ ቡድኑ የሴራ ተጋሪ መሆናቸው ነው።
ችግር ፈጣሪዎችን ቀያቸው አስቀምጠው ማዶ ላይ ያጓራሉ። ፊታቸው ያለው ክፋትና ጥፋት ለማየት ፈጽሞ አይፈልጉም። ክፋትና ቁርሾ ፍለጋ ይኳትናሉ። ምክንያቱም ትርፍ የሚያስገኘውና የንዋይ ጥማታቸውን የሚያረካው የሴራ ፖለቲካ ነው።
እነዚህ የፖለቲካ ነገዴዎች በድርጊትና በአስተሳሰብ አንድ ሆነው ሲያበቁ አንድ አይደለንም ይላሉ። ተገናኝተውና ሴራ ሰልቀው ሲያበቁ አልተገናኘንም ይላሉ። የመልዕክቶቻቸው ቀመር ሳይቀር አንድ ነው፤ የሚናገሩትና የሚተነትኑት ተመሳሳይ ሆኖ በገሃድ እየታየ እኛ ይህን አቋምና ሀሳብ አላረመድንም ይላሉ። “በፋሲካ የተዳረች ሁሌ ፋሲካ ይመስላታል” እንደሚባለው ጥፋት እና ግጭትን ሲዘሩ ሀገር ያንቀጠቀጡ ይመስላቸዋል ።
ራሳቸውን አዋቂ፣ ተንታኝ፣ መፍትሔ አፍላቂ የሆኑ ያህልም ይሰማቸዋል። የሌላው ዝምታ የነሱ ንግስና ሆኖ ይታያቸዋል። ሳይተኙ ቅቤ ያመነዥካሉ። ባህሪያቸው እና ውስጣዊ ፍላጎታቸው አንድ ስለሆነ አንዱ ለሌላው ያለውን ጥላቻ በጉያቸው ይዘው ለእኩይ ሴራ ይሰባሰባሉ፣ ይዶልታሉ፣ ህዝብ በድንቁርናቸው ያዋርዳሉ፣ ያስቀይማሉ።
ህዝብ ስለታገሰ ያላወቀ የሚመስላቸው እነዚህ አካላት፣ በስሙ የሚነግዱበት ማህበረሰብ ለሰላሙና ለልማቱ እየታገላቸው መሆኑን እንኳ ልብ የማይሉ ናቸው። በህዝብ ስም የሚነግዱበት ተራ ስሌት ግን አደባባይ እየወጣና እየከሰመ ነው፤ የሰሞኑ ድርጊት ያጋለጠው ይህን እዉነት ነው ሲሉ የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) መልእክታቸዉን አስተላልፈዋል፡፡