ልጆች እንዴት ከረማችሁ? ክረምቱን እንዴት እያሳለፋችሁት ነው? ይህንን የክረምት ወቅት በጨዋታ፣ በመዝናኛ ስፍራዎች፣ ለቀጣይ ትምህርታችሁ ዝግጅት በማድረግ እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ በክረምት ወቅት ራሳቸውን ለአደጋ በሚያጋልጥ ቦታ የሚያሳልፉ አንዳንድ ልጆች ይኖራሉ፡፡ ድንገተኛ ጎርፍ ሊከሰት ይችላል፡፡ ተቆፍረው ባልተደፈኑ ጉድጓዶች ውስጥ የዝናብ ውሃ ሊጠራቀም ይችላል፡፡ ልጆች፤ እነዚህ አካባቢዎች ላይ ካልተጠነቀቃችሁ ለአደጋ እንደምትጋለጡ ታውቃላችሁ አይደል? ጎበዞች፡፡ ያነጋገርናቸው ልጆች በዚህ ዙሪያ ያላቸውን ሀሳብ አካፍለውናል፡፡
ህጻን ዮሴፍ ሀይሉ ይባላል፡፡ ያገኘነው አንበሳ ግቢ ፓርክ ሲዝናና ነው፡፡ “የክረምት የእረፍት ጊዜዬን ወላጆቼ አንበሳ ግቢን ጨምሮ በተለያዩ ስፍራዎች እንድዝናና ያደርጉኛል፡፡ የዓድዋ ድል መታሰቢያንም ጎብኝቻለሁ፡፡ ቤተሰቦቼ ወስደው ከሚያዝናኑኝ በተጨማሪ ከሰፈር ጓደኞቼ ጋር ኳስ እና የተለያዩ ጨዋታዎችን እጫወታለሁ፡፡ በዘንድሮው ክረምት በምጫወትበት ወቅት ያጋጠመኝ አንድ ክስተት አለ፡፡ ክረምት እንደገባ ከጓደኞቼ ጋር ስጫወት ጫማዬን ጎርፍ ወሰደብኝ፡፡ ይህ የሆነው እየተጫወትን ባለበት ጊዜ ከባድ ዝናብ በመዝነቡ ነው። እኔና ጓደኞቼ ዝናቡ እስከሚያባራ ድረስ ትልልቅ ሰዎች ከተጠለሉበት ሱቅ ውስጥ በመግባት ተጠልለን አሳለፍነው፡፡ ዝናቡ ከቆመ በኋላ ወደቤታችን ስንሄድ በብዛት የመጣው ጎርፍ የአንድ እግር ጫማዬን ወሰደብኝ፡፡ እኔም በባዶ እግሬ ወደቤቴ ተመለስኩኝ፡፡ ወላጆቼም በዝናብ ወቅት ከቤት መውጣት እንደሌለብኝ መከሩኝ፡፡ ከዛን ቀን በኋላ ዝናብ ቀድሞ ከዘነበ ከቤት አልወጣም፡፡ እየተጫወትን መዝነብ ከጀመረ ደግሞ፤ ሁላችንም ወደቤታችን እየሮጥን እንሄዳለን፡፡” ብሏል፡፡
ህጻን ሲሳይ መላኩ በበኩሉ ከክረምት ጎርፍ ጋር በተያያዘ ያለውን ገጠመኝ ሲገልፅ፤ “ከሁለት ዓመታት በፊት ከጓደኞቼ ጋር ስሯሯጥ ለግንባታ በተቆፈረ ጉድጓድ ውስጥ ገብቼ አውቃለሁ። ከዚያን ጊዜ በኋላ አነስተኛ ኩሬ አካባቢ መንቀሳቀስ እና ውስጡ መግባት እፈራለሁ፡፡ ዝናብ ሲዘንብም ሆነ ከዘነበ በኋላ ወደውጭ አልወጣም፡፡
ምክንያቱም አንዳንድ ጎድጓዳ ስፍራዎች ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ውሀ ይዘው ስለሚቆዩ አካባቢው እስኪደርቅ በጥንቃቄ ነው የምንቀሳቀሰው፡፡” ሲል አብራርቷል፡፡
ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ አንዲት እናት ከክረምት ወቅት ጋር በተያያዘ በህጻን ልጃቸው ላይ የደረሰባቸውን አሳዛኝ አጋጣሚ እንዲህ ያስታውሳሉ፤ “ክረምት ሲመጣ መጥፎ ስሜት ነው የሚሰማኝ፡፡ ምክንያቱም ከሦስት ዓመት በፊት በኮልፌ ቀራኒዬ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ልዩ ስሙ ኮሽም በተባለ አካባቢ በጎርፍ አደጋ የስምንት ዓመት ዕድሜ ላይ ይገኝ የነበረው ልጄ ሊጫወት እንደወጣ ሳይመለስ መቅረቱ ልቤን በሀዘን ሰብሮታል፡፡” ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ደሳለኝ ፉፋ ለልጆች ባስተላለፉት መልዕክት “ልጆች፤ በክረምት ወቅት ዝናብ ይጥላል፡፡ ዝናቡ ደግሞ ጎርፍ ያስከትላል፡፡ ጎርፍ ደግሞ ተገቢ ጥንቃቄ ካልተደረገበት በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ያስከትላል፡፡ አንዳንድ ወንዞች ደግሞ በክረምት ወቅት ይሞላሉ፡፡ የዋና ችሎታ ሳይኖራችሁ እንዋኛለን ብላችሁ መግባት የለባችሁም፡፡ እንዲሁም ማዕድን ለማውጣት የተቆፈሩ ጉድጓዶች በክረምት ወቅት በጎርፍ ስለሚሞሉ ልጆች እንዲህ አይነት ጉድጓዶች ውስጥ ትንሽ መስሏችሁ ከመግባት ልትቆጠቡ ይገባችኋል፡፡ ሌላው በከባድ ዝናብ የሚፈጠር የሜዳ ጎርፍን በመናቅ ጎርፍ ውስጥ ከመግባት ራሳችሁን መጠበቅ አለባችሁ” ብለዋል፡፡
በለይላ መሀመድ