• የፈጣን አውቶቡስ አገልግሎት በዓለም ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጀመረው እ.ኤ.አ በ1974 በብራዚል ኩሪቲባ ከተማ ነው የናይጄሪያዋ ዋና ከተማ ሌጎስ ደግሞ ከአፍሪካ ቀዳሚ በመሆን እ.ኤ.አ በ2008 አገልግሎቱን ማስጀመር ችላለች ፡፡
የፈጣን አውቶቡስ አገልግሎት በዓለም ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጀመረው እ.ኤ.አ በ1974 በብራዚል ኩሪቲባ ከተማ ሲሆን የናይጀሪያዋ ዋና ከተማ ሌጎስ ደግሞ ከአፍሪካ ቀዳሚ በመሆን እ.ኤ.አ በ2008 አገልግሎቱን ያስጀመረች ሀገር ናት ፡፡
መዲናችን አዲስ አበባ የፈጣን አውቶቡስ መተላለፊያ መስመር ለማስጀመር ያግዛል የተባለውን የፈጣን አውቶቡስ መተላለፊያ ስርዓት /BRT 2/ የተሰኘ ፕሮጀክት ተግባራዊ ለማድረግ በእንቅስቃሴ ላይ ትገኛለች ፡፡
ይህ የመተላለፊያ መስመር /Bus Rapid Transit / የህዝብ ማመላለሻ ስርዓት ሲሆን በትራፊክ መጨናነቅ ምክንያት የሚፈጠሩ መዘግየቶችን ለመቀነስ አውቶቡሶች ብቻ የሚጠቀሙበት ልዩ መስመር ነው። በመስቀለኛ እና በመገናኛ መንገዶች ላይ ከሌሎች ተሽከርካሪዎች ቅድሚያ እንዲያልፉ ዕድል የሚሰጥ ነው። ዓላማው ቅልጥፍና እና ፍጥነትን የሚያጣምር የትራንስፖርት ሥርዓት መገንባት ሲሆን በዝቅተኛ ዋጋ የሚከናወን ነው። አውቶቡሶቹም በተለዩላቸው መስመሮች ውስጥ የሚንቀሳቀሱ በመሆኑ በሌሎች ተሽከርካሪዎች ላይ የሚፈጠርን የትራፊክ መጨናነቅ ይቀንሳል።
ፈጣን የአውቶቡስ መተላለፊያ መስመሩ. ከአዲስ አበባ ከተማ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በሚገባ የሚዋሃድ ሲሆን ከወጪ አንፃር ከሜትሮ ወይም ከቀላል ባቡር ትራንዚት ስርዓት ግንባታ ጋር ሲነፃፀር በጣም ርካሽ የሚባልና፤ አሁን ካለው ቀላል ባቡር ትራንዚት ስርዓት ጋር በቀላሉ መቀናጀት የሚችል ነው ፡፡
የአዲስ አበባ ፈጣን አውቶቡስ መተላለፊያ መስመር ከፍተኛ አቅም ያላቸውና ረጅም ርቀት የሚጓዙ አውቶቡሶችን ለማስተናገድ የተነደፈ ነው። ተሳፋሪዎች በሚበዙበት የስራ መግቢያና መውጫ ሰዓት ከመደበኛ አውቶቡሶች የበለጠ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል ።
የአዲስ አበባ ቢ. አር. ቲ. መስመር የኤሌክትሪክ አውቶቡሶችን የሚጠቀም በመሆኑ ሙሉ በሙሉ ከአየር ብክለት ነፃ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የመንገደኞችን አውቶቡስ መጠበቂያ ጊዜ ከመቀነሱም በላይ የቅድመ ክፍያ ትኬት ስርዓት መኖሩ በአጠቃላይ ለትራንስፖርት አገልግሎቱ መቀላጠፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል። በተጨማሪም አውቶቡስ መስመሩ የትራፊክ ደህንነትን ባረጋገጠ መልኩ በእግረኛ ማቋረጫዎች ላይ ዲጂታል የትራፊክ ምልክቶችን ያካተተ ነው፡፡
የፈጣን አውቶቡስ መተላለፊያ መስመር (ቢ.አር.ቲ.) ፕሮጀክት ሁለት ዋና ዋና ክፍሎች ያሉት ሲሆን የመጀመሪያው የቢ.አር.ቲ ኮሪደር ግንባታ ፣ የአውቶቡስ ጣቢያዎች እና ዴፖ ግንባታ ሥራዎችን ያካትታል። ሁለተኛው የቢ.አር.ቲ ፍሊት አቅርቦትን እና ብልህ የትራንስፖርት ሥርዓት /ITS/ ጨምሮ ዘላቂ የቢ አር ቲ ሥራዎችን ማቋቋምን የያዘ ነው፡፡
ቢ2 የተሰኘው የፈጣን አውቶቡስ መተላለፊያ መስመር መነሻውን ዳግማዊ ምኒልክ አደባባይ አድርጎ ጀሞ 3 የመስመሩ የመጨረሻ መዳረሻ ይሆናል። ፕሮጀክቱ በአጠቃላይ 15 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር ርዝመት ሲኖረው የሚያልፍባቸው አካባቢዎችም፡- ከጊዮርጊስ በአንዋር መስጅድ ወደ ተክለ ኃይማኖት በመታጠፍ ሜክሲኮ – ቄራ – ጎፋ ገብርኤል – ጀርመን አደባባይን በማቋረጥ በጀሞ ሚካኤል አድርጎ ጀሞ 3 የሚደርስ ይሆናል ፡፡
227 የኤሌክትሪክ አውቶቡሶችን የሚያስተናግድ የተሽከርካሪ ማቆሚያ ስፍራ እና የአስተዳደር ህንፃን አካትቶ የያዘ እንዲሁም ለአውቶቡስ ጥገና እና የኤሌክትሪክ ኃይል ለመሙላት የሚያገለግል ደረጃውን የጠበቀ ግዙፍ ዴፖ፤ ጀሞ በሚገኘው የአንበሳ አውቶቡስ ጋራዥ ውስጥ ይገነባል፡፡
ለፕሮጀክቱ ከሚያስፈልገው አጠቃላይ ወጪ 85 ሚሊየን ዩሮ በፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ የሚሸፈን ሲሆን ቀሪው ከ70 እስከ 100 ሚሊየን ዩሮ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይሸፈናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ፕሮጀክቱን ለመተግበር 1ኛ. የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ለቢ. አር. ቲ ፍሊት፣ ሲስተም እና ኦፕሬሽን 2ኛ. የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ለመሠረተ ልማት ዲዛይን እና ሲቪል ስራዎች እንደ አስፈፃሚ ኤጀንሲ ሆነው ያገለግላሉ ።
ከቄራ እስከ ምኒልክ አደባባይ (ጊዮርጊስ) የሚደርሰውና 20 የአውቶቡስ ጣቢያዎችን አካትቶ የያዘው ኮሪደር አጠቃላይ 8 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን በ‘ቻይና ኮንስትራክሽንና ኮሙዩኒኬሽን ካምፓኒ (cccc)’ የሚገነባ ነው ፡፡ የፕሮጀክቱ ግንባታም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንደሚጀመር ይጠበቃል።
ቀሪው የፕሮጀክቱ ክፍል ግንባታው በ56 ነጥብ 5ሚሊዮን ዶላር ገደማ እና በ554 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚካሄድ ሲሆን በጨረታ ሂደት ላይ ነው፡፡
በጀሞ የሚገነባው የጥገና ማዕከልና የኤሌክትሪክ አውቶቡስ ዴፖ በቻይና ሲቪል ኢንጂነሪንግ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን (CCEC) አማካኝነት በ15 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላርና እና በ148 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚገነባ ነው። የግንባታ ቁጥጥርና ማማከር ሥራውን ሲስትራ ከኮር ኮንሰልቲንግ መሐንዲሶች ኃ.የተ.የግ.ማ. በጥምረት የሚያካሂዱት ሲሆን ለዚህም ከ3ሚሊዮን ዩሮ በላይና 148 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጪ ተይዞለታል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጀት የሚገነባውና ከቄራ እስከ ጀሞ ያለው መስመር በጨረታ ሂደት ላይ ሲሆን ግንባታው በተያዘው በጀት ዓመት 3ኛ ሩብ ዓመት ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በተፈረመው የኮንትራት ውል መሰረት የኮሪደር እና የአውቶቡስ ጣቢያዎች ግንባታ ስራው ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ባሉት 730 ቀናት ውስጥ እንዲሁም የዴፖ ግንባታው በ540 ቀናት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
ፕሮጀክቱ የተነደፈው ህንፃዎችና ሌሎች መሠረተ ልማቶች ላይ ሊደርስ የሚችለውን አሉታዊ ተፅዕኖ መቀነስን ታሳቢ በማድረግ ነው። ይሁን እንጂ በአንዳንድ አካባቢዎች በመንገዱ በሁለቱም አቅጣጫዎች በኩል ያሉ ሕንፃዎችን የሚነካበት ሁኔታ ይኖራል። በአሁኑ ወቅት መስመሩ በሚያልፍባቸው አካባቢዎች የወሰን ማስከበር ስራው ተጠናቅቆ የካሳ ክፍያ የተፈጸመ በመሆኑ ተጨማሪ የማፍረስ ሂደት የሚኖርበት እድል አነስተኛ ነው ፡፡
ይህ የታቀደው የፈጣን አውቶቡስ መተላለፊያ መስመር ግንባታ የከተማዋ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች በስፋት እንዲጠቀሙበት ታሳቢ የተደረገ የብዙሃን ትራንስፖርት መስመር ነው። የመስመር ዝርጋታው ሙሉ ለሙሉ ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር በአዲስ አበባ ከተማ የሚታየውን የትራፊክ መጨናነቅ ለመቅረፍና ዘመናዊ የብዙሃን ትራንስፖርትን ለማስፋፋት ትልቅ እገዛ ይኖረዋል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡