ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልዕክት ዛሬ ማለዳ የከተማ አስተዳደራችን በሰጠው ልዩ ትኩረት እና ቁርጠኝነት ለ30 ሺህ የከተማችን ወጣቶች እና ሴቶች አዲስ የስራ ዕድል ፈጥረናል ሲሉ ገልጸዋል።
አዲስ አበባን እንደ ስሟ ዉብ አበባ የማድረግ ስራችን የነዋሪዎቿንም ኑሮ እና አኗኗር በመለወጥ ጭምር ነዉ ብለዋል።
ዛሬ ወደ ስራ ያስገባናቸዉ እነዚህ አዲስ ስራ ጀማሪዎች፣ ቀደም ሲል በተለያዩ መድረኮች ስንወያይ የስራ ዕድል ጥያቄ የነበራቸዉ ወጣቶችና ሴቶች ናቸዉ ሲሉም ገልጸዋል።
የስራ ዕድል ተጠቃሚዎቹ በኢንተርፕራይዝ ተደራጅተው በከተማ ግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኮንስትራክሽን፣ በንግድ፣ በአገልግሎትና በሌሎችም አዋጭ ዘርፎች ላይ በልዩ ሁኔታ በማሰማራት ዛሬ ስራ አስጀምረናል ብለዋል።

ይህ በከተማችን በስፋት እየተተገበረ ያለዉ የአንድ ጀምበር የስራ ዕድል ፈጠራ ንቅናቄ በቀጣይነት በልዩ ትኩረት እየተደገፈ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ሲሉም አረጋግጠዋል።
አስተዳደራችን በቀጣይም በላባቸዉ ፍሬ የሚኖሩ ፣ ሥራ ፈጣሪ ፣ ታታሪ ዜጎችን በሁሉም መስክ መደገፉን አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
በሥራ ዓለም የበለጠ ዉጤታማ እንዲሆኑ በማድረግ የጀመርነዉን የብልጽግና ጉዞ በሙሉ ቁርጠኝነት እውን ለማድረግ የተጀመሩ ተግባራት በከተማችን ይበልጥ ተጠናክረዉ የሚቀጥሉ ይሆናል በማለትም አክለዋል።
ዉድ የሥራ ዕድሉ የተፈጠረላችሁ ወጣቶች እና ሴቶች አስተዳደራችን ለእናንተ አስፈላጊዉን ድጋፍ እና ክትትል የሚያደርግላችሁ ሲሆን፣ በተፈጠረዉ እድል በአግባቡ በመጠቀም ጠንክራችሁ በመስራት የራሳችሁን፣ የከተማችሁን ታሪክ የምትቀይሩ ዉጤታማ ዜጎች መሆን ይጠበቅባችኋል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።