AMN – ሐምሌ 19/2018 ዓ.ም
በሀገራችን የእናቶችን ሕይወት ከሚቀጥፉ ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል ከወሊድ ጋር ተያይዞ የሚከሰት ደም መፍሰስ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል።
በአበበች ጎበና የእናቶች እና ህጻናት ሆስፒታል የማህጸን እና ጽንስ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር አህመድ አባቡ፣ ይህን አደገኛ ችግር በጊዜ በመለየት የእናቶችን ህሕይወት እንዴት መታደግ እንደሚቻል ከኤ ኤም ኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
አንድ እናት ከወለደች በኋላ የተለያዩ ችግሮች ሊከሰቱ ቢችሉም፣ በጊዜ ክትትል ተደርጎባቸው መታከም ከቻሉ መፍትሔ ማግኘት እንደሚቻል የሕክምና ባለሙያው ይገልጻሉ።
በተለይም ከወሊድ በኋላ የሚከሰት የደም መፍሰስ በጊዜ ካልተደረሰበት አስከፊ መዘዝ እንደሚያመጣ ነው ያስጠነቀቁት።

በቅድመ ጥንቃቄ እና በተገቢው ህክምና ሕይወትን ማተርፍ ይቻላል የሚሉት ዶክተር አህመድ አባቡ የችግሩን መንስኤዎች እና አስቸኳይ መፍትሔዎችን አስረድተዋል።
የደም መፍሰስ ዓይነቶች እና መንስኤዎች
እንደ ዶክተር አህመድ አባቡ ገለፃ ፣ ከወሊድ በኋላ የደም መፍሰስ ችግር በሁለት መልኩ ማለትም ማህጸን በመጠቀም ወይም ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ ከወለዱ በኋላ እና በኦፕሬሽን (ቀዶ ጥገና) ከወለዱ በኋላ ሊከሰት ይችላል።
ከወሊድ በኋላ ለሚከሰት የደም መፍሰስ ዋና ዋና ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
1. የማህጸን ጉዳት
ህፃኑ በሚወለድበት ጊዜ በማህጸን ክፍሎች ላይ የሚደርስ መሠንጠቅ ሲኖር የሚከሰት ሲሆን ፣ ይህም በጊዜ ታክሞ ከተሰፋ ሊቆም እንደሚችል ዶክተር አህመድ አባቡ ገልጸዋል።
2. የማህጸን መላላት
የማህጸን መላላት ማለት ማህጸን ወደ ቀድሞ ቦታው አለመለስ ሲሆን ፣ እንደ ሕክምና ባለውያው ገለፃ ይህ ችግር ብዙውን ጊዜ መንታ በወለዱ፣ ረጅም ሰዓት ባማጡ ወይም አካለ ትልቅ ልጅ በወለዱ እናቶች ላይ በብዛት ይታያል።
ይህም ማሳጅ በማድረግ እና ተስማሚ መድኃኒቶችን በመስጠት ወደ ቦታው መመለስ እንደሚቻል አስረድተዋል።

3. እንግዴ ልጅ ከውስጥ መቅረት
ከወሊድ በኋላ የእንግዴ ልጅ የተወሰነ ክፍል ወይም ከልጁ ጋር የተያያዙ ነገሮች ከውስጥ ሲቀሩ የሚከሰት ሲሆን ፣ እነዚህን ነገሮች በማስወገድ ደሙ እንዲቆም ማድረግ ይቻላል።
4. ሆድ ውስጥ ደም መከማቸት (ከኦፕሬሽን በኋላ)
በቀዶ ጥገና ወቅት ደም በሆድ ውስጥ ስለሚጠራቀም በቀላሉ ለመለየት አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል የማህጸን እና ጽንስ ስፔሻሊስቱ ዶክተር አህመድ አባቡ ጠቅሰዋል።
ስለዚህ ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግ ፣ በጊዜው ተለይቶ ድጋሚ ኦፕሬሽን በመስራት የሚደማውን አካል መቆጣጠር ያስፈልጋል ብለዋል።
ሊደረጉ የሚገቡ ሕክምናዎች
ችግሮቹን በጊዜው ለይቶ ማወቅ ለህክምናው ስኬት ትልቅ ሚና አለው የሚሉት ዶክተር አህመድ አባቡ፤ እንደ አስፈላጊነቱ ደም መስጠት፣ ማህጸን ወደ ቦታው መመለስ እና መድኃኒቶችን መጠቀም እንደሚገባ አስረድተዋል።
አብዛኛዎቹ ተፈጥሯዊ የደም መፍሰስ ችግሮች ከወለዱ በኋላ በራሳቸው የሚመለሱ ቢሆንም ፣ የከፋ ችግር ሲያጋጥም የህክምና ባለሙያዎች አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ ሊደርጉ እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት።

የማህጸን እና ጽንስ ስፔሻሊስቱ ዶክተር አህመድ አባቡ ፣ አንድ እናት ከወለደች በኋላ ሊከሰቱ የሚችሉ እና ጥንቃቄ ሊደረግባቸው የሚገቡ አደገኛ ምልክቶችንም ጠቅሰዋል።
ከወሊድ በኋላ እየጨመረ የሚመጣ የደም መፍሰስ፣ ከማህጸን ሽታ ያለው ፈሳሽ መውጣት ፣ ብርድ ብርድ ማለት እና ማንቀጥቀጥ ፣ ትኩሳት ፣ ከባድ የሆነ ራስ ምታት ፣ የሚጥል በሽታ ዓይነት ስሜቶች መሰማት ምልክቶቹ መሆናቸውን ዘርዝረዋል።
እነዚህ ምልክቶች በሚታዩበት ጊዜ እናትየው ሳትዘናጋ ወዲያውኑ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ተገቢውን የህክምና እርዳታ ማግኘት እንደሚኖርባትም አጽኖት ሰጥተዋል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ