የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ለአፍሪካ የንግድ ቀጠና መጠናከር ወሳኝ ነው

You are currently viewing የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ለአፍሪካ የንግድ ቀጠና መጠናከር ወሳኝ ነው

AMN – የካቲት 25/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት መሆን ከሀገራዊ ፋይዳው ባለፈ፣ ለቀጠናውና ለመላው የአፍሪካ ሀገራት ጠንካራ የንግድ ትስስር ለመፍጠር ወሳኝ መሆኑን አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ፡፡

ይህ የተገለጠው በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ (AASTU) እየተካሄደ በሚገኘውና “የኢትዮጵያ የባህርና የወደብ መዳረሻ ጥያቄ፦ ታሪካዊ መብትና ህጋዊ የይገባኛል ጥያቄ” በሚል መሪ ቃል በተዘጋጀ የፓናል ውይይት ላይ ነው።

በውይይቱ ላይ የተገኙት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት መሆኗ ነፃና ጠንካራ የንግድ ቀጠና ለመፍጠር መሰረት መሆኑን ገልጸዋል።

አምባሳደሩ አክለውም፣ ኢትዮጵያ ለቀጠናው ሰላምና መረጋጋት እያበረከተች ያለውን ከፍተኛ ሚና ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ሊረዱት እንደሚገባ ጠቁመው፤ የባህር በር ጥያቄዋ ስኬታማ መሆን የጋራ ተጠቃሚነትን እንደሚያረጋግጥ አስገንዝበዋል።

የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ደረጀ እንግዳ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ዩኒቨርሲቲው በሀገራዊ ጥቅሞች ላይ ያተኮሩ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት የዘመኑን ትውልድ አደራ ለመወጣትና የሀገርን ጥያቄ ለማሳካት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የውይይት መነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት የምጣኔ ሀብትና የፖለቲካ ምሁሩ ዱጋሳ ሙሉጌታ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ የባህር በር ያጣችበት ሁኔታ ታሪካዊና ህጋዊ መሰረት የሌለው መሆኑን አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ የባህር በርን ለማግኘት በሰላማዊ መንገድ፣ በትብብር መርህ፣ እና በ“ስጥቶ መቀበል” መርህ ላይ የተመሰረተ መሆኑን አብራርተዋል።

ወደብ ማጣት በኢትዮጵያ ላይ ያስከተለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመቀነስ የጥያቄውን አግባብነት ተረድቶ በሕብረት መቆም እንደሚገባ በመድረኩ ተመላክቷል።

የባህር በር ጥያቄውን ከግብ ለማድረስም በዲፕሎማሲ፣ በወታደራዊ ዝግጁነት፣ በውስጥ አቅም ግንባታና በሕዝብ አንድነት ላይ የተመሰረተ የተቀናጀ ርብርብ እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።

በንጉሱ በቃሉ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review