ህጻናት እና የስክሪን አጠቃቀም፦ የወቅቱ ፈታኝ የቤት ስራ!

You are currently viewing ህጻናት እና የስክሪን አጠቃቀም፦ የወቅቱ ፈታኝ የቤት ስራ!

AMN — መጋቢት 21/2018 ዓ.ም

“ልጄ ስልክ ካልያዘች ምግብ አትበላም…”፣ “ልጄ ሞባይል ካላየ አይተኛም…” የሚሉ ንግግሮች በቤታችን የተለመዱ ሆነዋል። ነገር ግን ይህ “የዝምታ መድኃኒት” የሆነው ስክሪን በልጆቻችን ዕድገት ላይ ምን ተፅዕኖ እያመጣ ይሆን?

በቅርቡ የወጡ ዓለም አቀፍ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ ህጻናት ለረጅም ጊዜ በስክሪን ፊት ብቻቸውን ማሳለፋቸው ከፍተኛ ጉዳት አለው። በተለይ እንደ እንግሊዝ እና አውስትራሊያ ያሉ ሀገራት ከ16 ዓመት በታች ያሉ ህጻናት ማህበራዊ ሚዲያ እንዳይጠቀሙ በህግ ለመከልከል እየሰሩ ይገኛሉ።

ልጆቻችን ስክሪን ፊት ብቻቸውን ሲሆኑ ምን ይከሰታል?

የእንቅልፍ መዛባት አንዱ ነው የስክሪን ብርሃን የእንቅልፍ ሆርሞንን በማስተጓጎል የልጆችን ዕረፍት ይነሳል። ሌላኛው የዕድገት መዘግየት ማለትም ከአካላዊ እንቅስቃሴ እና ከሰዎች ጋር ካለ ግንኙነት ስለሚያርቃቸው ማህበራዊ ክህሎታቸው እንዲቀንስ የሚያደርጋቸው ሲሆን በተጨማሪም የባህሪ ለውጥ ማሳየት ስልኩ ሲወሰድባቸው ለከፍተኛ ብስጭት እና ለደስታ ማጣት ይዳረጋሉ።

ታዲያ ለዚህ ችግር ባለሙያዎች ምን ይመክራሉ?

ዕድሜን ያገናዘበ አጠቃቀም ማለትም ከ2 ዓመት በታች ያሉ ህጻናት ስክሪን ባያዩ ይመከራል። ከ2-5 ዓመት ደግሞ በቀን ከአንድ ሰዓት ባልበለጠ ጊዜ፣ ያውም ከወላጅ ጋር ሆነው እንዲያዩ ይመከራል ።

ህጻናት ብቻቸውን ከመመልከት ይልቅ ከወላጆቻቸው ጋር አብሮነት ትምህርታዊ ቪዲዮዎችን ቢመለከቱ የተሻለ የዕውቀት ዕድገት ያመጣሉ ተብሎ ይታመናል ።

ወላጆች ስልክ ላይ አፍጥጠን ልጆቻችንን “አትመልከቱ” ማለት አንችልም። ከልጆቻችን ጋር ስንሆን ትኩረታችንን ሙሉ በሙሉ ለእነሱ በመስጠት አርአያ መሆን አለብን።

በተለይ በምግብ ሰዓት ስልክ ከመስጠት ይልቅ አማራጭ ጨዋታዎች ማለትም ታሪኮችን ማንበብ ወይም ቀለል ያሉ ጨዋታዎችን መጫወት እንደሚገባ የዘርፉ ምሁራን መፍትሄ ይሆናል ባይ ናቸው ።

ታዲያ የእርስዎ ተሞክሮ ምንድነው?

በቤትዎ ውስጥ የልጆችን የስክሪን ሰዓት እንዴት ይቆጣጠራሉ? በዚህ ረገድ የገጠማችሁ ፈተና አለ? ወይስ የተጠቀማችሁት ውጤታማ መፍትሄ?

ሀሳብዎን ያካፍሉን፤ ለሌሎች ወላጆችም እንዲደርስ ይህንን መረጃ ያጋሩ/ሼር/ ያድርጉ።

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review