ለትውልድ እየተገነባች ያለች መዲና

You are currently viewing ለትውልድ እየተገነባች ያለች መዲና

AMN- ጥቅምት 17/2019 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፉት ዓመታት የከተማዋን ገጽታ በመቀየር የነዋሪዎችን ኑሮ ማሻሻል ያስቻሉ በርካታ የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎችን እውን አድርጓል።

ከእነዚህም መካከል የቀጨኔ፣ አምባሳደር፣ ጊዮን፣ ኢሬቻ፣ ባምቢስ የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት የከተማዋን ሁለገብ ትራንስፎርሜሽን በማሳየት ረገድ ከፍተኛ ትርጉም አለው፡፡

351 ሄክታር አጠቃላይ ስፋት እና 10 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለው ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት፤ ከተማዋን የኑሮ ማዕከል ብቻ ሳይሆን ለትውልድ የሚተርፍ ውብ፣ አረንጓዴ እና ዘመናዊ የከተማ ከባቢ ለመፍጠር የተያዘውን ራዕይ በተግባር የሚያሳይ ነው።

ይህ ፕሮጀክት ከዚህ ቀደም በከተማዋ ከተከናወኑ የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎች ጋር የተሳሰረ ነው። ለዜጎች ምቹ የሆኑ ሰፋፊ እግረኛ መንገዶች፣ የብስክሌት መተላለፊያዎች እና የተቀናጁ የትራንስፖርት መሠረተ ልማቶችን አካቷል።

የመኪና ማቆሚያ ስፍራዎች እና የኤሌክትሪክ መኪና መሙያ ማዕከላት መካተታቸው የፕሮጀክቱን ዘመናዊነትና መጪውን ጊዜ የሚዋጅ የከተማ ልማት ሥራ እየተከናወነ እንዳለ አመላካች ናቸው።

ልማቱ የሰዎችን ማኅበራዊ ሕይወት የሚያቀናጅ ሲሆን ፣ የልጆች መጫወቻ ስፍራዎች፣ ፕላዛዎችና አምፊ ቲያትሮች፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎች፣ እንዲሁም ማራኪ የውሃ ትርዒት ማሳያዎች ተካተውበታል፡፡ እነዚህም ለቤተሰቦች፣ ለወጣቶችና ለጎብኚዎች የመዝናኛ እና የማኅበራዊ ግንኙነት ማዕከላት በመሆን የከተማዋን ማኅበራዊ ትስስር ያጠናክራሉ።

በተጨማሪም የወንዝ አስተዳደርን፣ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎችን እንዲሁም ሰፋፊ አረንጓዴ ስፍራዎችን ከከተማው ውበት ጋር በማቀናጀት ረገድ ፕሮጀክቱ ትልቅ አርአያ የሚሆን ሥራ ነው።

የተበላሹ የወንዝ ዳርቻዎችን ወደ አረንጓዴ እና ምቹ ስፍራዎች በመቀየር የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚደረገውን ጥረት አጠናክሮታል። ልማቱ ማህበራዊ ገጽታውን ከመቀየር ባለፈ ቀደም ሲል በወንዝ ዳርቻው አካባቢ ይኖሩ ለነበሩ ነዋሪዎች ቅድሚያ የሰጠ የሥራ ዕድልም ፈጥሯል።

በስፍራው በተፈጠሩት የተለያዩ የንግድ እና የአገልግሎት መስኮች ነዋሪዎች ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። የኢኮኖሚ ዕድገቱ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ያካተተ እንዲሆን መደረጉ የከተማ አስተዳደሩን ዕድገት ፍትሃዊ የማድረግ ፖሊሲ ያንጸባርቃል።

የቀጨኔ፣ አምባሳደር፣ጊዮን-ኢሬቻ፣ ባምቢስ የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ለአገልግሎት መብቃት፤ የመንግሥት እና የከተማ አስተዳደሩ ራዕይ ለዛሬውም ሆነ ለሚቀጥሉት ትውልዶች ውብ፣ ምርታማ እና ሁሉንም አካታች ከተማ መገንባት መሆኑን በግልጽ ያሳያል።

አዲስ አበባ የሰዎቿን ክብር የሚመጥን፣ ለኑሮ እጅግ ተስማሚ እና በአፍሪካ የከተሞች ልማት አርያነቷን የሚያረጋግጥ አንጸባራቂ ማሳያ ነው።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review