“ሰንደቃችን የሁለንተናዊ ብልጽግናችን ከፍታ ማሳያ፤ የወል ትርክታችን ምልክት ነው” – የመንግስት ኮሙኒኬሽን ሚኒስትር እናትዓለም መለሰ

AMN – ጥቅምት 2/2019 ዓ.ም

19ኛው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ቀን በመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት “ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ መግባባት እና አንድነታችን!” በሚል መሪ መልእክት ተከብሯል። በመድረኩ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር እናትዓለም መለሰ እንደገለጹት፤ ሰንደቅ ዓላማችን የትናንት ማንነታችንን ከነገው የብልጽግና ርዕያችን ጋር ያጋመደ የአንድነታችን ትርክት ነው ብለዋል።

ሚንስትሯ አክለውም የጋራ ማንነታችን የሆነው ሰንደቃችን በከፍታ እንዲውለበለብ ሁለንተናዊ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በሁሉም መስኮች በትጋት እና በሀገር ፍቅር ስሜት መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

በሀገራችን ረጅም ታሪክ ውስጥ ሰንደቅ ዓላማችን በታላላቅ የድል ገድሎች፣ በውድ የህይወትና የላብ መስዋዕትነት የደመቀ ብሔራዊ መገለጫችን ነው ያሉ ሲሆን ፤የሀገራችንን ብሔራዊ ጥቅም እና ደኅንነት ለማስጠበቅ በየጦር ግንባሩ ከተከፈለው መስዋዕትነት ባሻገር፤ በስፖርታዊ መድረኮችም በጀግኖች አትሌቶቻችን አማካኝነት የሰንደቅ ዓላማችን ክብር እና ከፍታ ደጋግሞ ተንጸባርቋል ሲሉ አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በሁለንተናዊ ከፍታ ላይ እንዲውለበለብ ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የጋራ ጥረትና ድል ይጠበቃል ያሉት ወ/ሮ እናታለም ዕዳን ለትውልድ ሳናሸጋግር የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ፣ የኢንዱስትሪ ምርታማነትንና ተወዳዳሪነትን ማሳደግ፣ የተፈጥሮ ሀብቶቻችንን በአግባቡ በመጠቀም ሁለንተናዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ እና ብሔራዊ ጥቅማችንን ማስጠበቅ የሰንደቃችንን ከፍታ የሚያረጋግጡ ሀገራዊ ኃላፊነቶች ናቸው ብለዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review