AMN – ሐምሌ 22/2018 ዓ.ም
የአፍሪካውያን የጋራ ቤት የሆነችው አዲስ አበባ 49ኛውን የአፍሪካ ህብረት የሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ በደማቅ ሁኔታ እያስተናገደች ትገኛለች።
የዲፕሎማሲ መዲናዋ አዲስ አበባ ፣ የአፍሪካ ወንድሞቿንና እህቶቿን በለመደችው አፍሪካዊ ፍቅርና ክብር ፣ በአዲስ የልማት ምዕራፍ ልዩ ውበት በተላበሰችበት ማራኪ ገፅታዋ ተቀብላለች።
የተከናወኑት የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻዎች ልማት ሥራዎች ለከተማይቱ አዲስ ህይወት፣ ድምቀትና ግርማ ሞገስ ሰጥተዋታል።
የኮሪደር ልማት ሰፊና ፅዱ የእግርኛ መንገዶችን ፣ ሰፋፊ የተሸከርካሪ መንገዶችና የመንገድ ላይ መብራቶች እንዲሁም ውብ የሕዝብ አደባባዮችን በመፍጠር አዲስ አበባን እውነተኛ የመላው አፍሪካ ሜትሮፖሊታን ከተማ እያደረጋት ይገኛል።
ቀደም ሲል ተዘንግተው የነበሩ የወንዝ ዳርቻዎች ዛሬ ተለውጠው ለዓይን የሚማርኩ አረንጓዴ ስፍራዎች ፣ የሕዝብ መዝናኛዎችና የውበት ማዕከላት ሆነዋል፡፡
በመዲናዋ የተከናወነው ይህ ስር ነቀል ለውጥ አዲስ አበባ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ትልልቅ ጉባኤዎችን በከፍተኛ ብቃት ለማስተናገድ ያላትን አቅም በከፍተኛ ደረጃ አሳድጎታል።
ዘመናዊው የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ለዲፕሎማቶችና እንግዶች ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ፅዱና ዘመናዊ የከተማ ከባቢን ፈጥሯል። የጉባኤው ተሳታፊዎች የአፍሪካን የእድገትና የዘመናዊነት ተስፋ አዲስ አበባ ላይ በአይናቸው እንዲመለከቱ እድልም የሚፈጥር ነው።

የአፍሪካ ወንድሞች በየደረሱበት፣ በሆቴሎችና በስብሰባ ማዕከላት የሚያገኙት ምቹ መስተንግዶ አፍሪካዊ የወንድማማችነት መንፈስ እያዳበረላቸውም ይገኛል። አዲስ አበባም ምርጧ ፓን አፍሪካኒስት መዲና መሆኗን በተግባር እያረጋገጠች ትገኛለች።
የአፍሪካ ህብረት የሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት የወቅቱ ሊቀ መንበርና የቡሩንዲው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤድዋርድ ቢዚማና አዲስ አበባ የፓን አፍሪካኒዝም ህያው ምልክት ናት ሲሉ መስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
ሊቀ መንበሩ 49ኛውን የምክር ቤቱን መደበኛ ስብሰባ ሲከፍቱ ትናንት ባደረጉት ንግግር፤ ስብሰባውን እያስተናገደች ለምትገኘው ኢትዮጵያና ጥሩ አቀባበል ላደረገልን የኢትዮጵያ ህዝብ ምስጋና አቀርባለሁ ብለዋል።
የአዲስ አበባ ለውጥ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው አፍሪካ ኩራትና ማሳያ ነው። በሀገር በቀል እውቀት እየተከናወነ ያለው የወንዝ ዳርቻዎችና የኮሪደር ልማት አፍሪካውያን በራሳቸው አቅምና እይታ ከተሞቻቸውን እንዴት ማደስና ማዘመን እንደሚችሉ በአርአያነት ያገለግላል።
በታደሠ ሽፈራው