AMN- ጥቅምት 3/2019 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተቋም ግንባታንና የዲጂታል አገልግሎትን በማቀናጀት ባከናወናቸው ተግባራት ከ1 ሚሊዮን በላይ ዜጎች አገልግሎት ማግኘታቸውን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የበጀት ዓመቱን የ1ኛ ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ማጠቃለያን አስመልክቶ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሰጡት ማጠቃለያ ፤ የተቋም ግንባታና የሕዝብ እርካታ ዋናው የሥራ መለኪያ መሆናቸውን አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።

ከኢንቨስትመንትና የልማት ሥራዎች ጎን ለጎን የተቋም ግንባታና የዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥን በማቀናጀት ሕዝብን በታማኝነት ማገልገል ዋናው ትኩረት መሆኑን ተናግረዋል።
አስተዳደሩ በዘርፉ ባከናወናቸው የአፈጻጸም ጉድለት ላለባቸው አካላት ጥብቅ ሕጋዊ እርምጃዎች መወሰዱንም ገልጸዋል።

ከአገልግሎት አሰጣጥ አንጻር ከዚህ ቀደም ከነበሩት በተጨማሪ በዚህ ክረምት ብቻ ወደ 23 የሚጠጉ አገልግሎቶች ዲጂታላይዝድ ተገርገው ወደ “መሶብ” አንድ ማዕከል መግባታቸው ተገልጿል።
የመሶብ ዲጂታል የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ወደ 1 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች አገልግሎት ማግኘት የቻሉ ሲሆን፣ ከተገለጋዮች የተሰበሰበው መረጃ እንደሚያሳየው የ99 በመቶ ሕዝብ እርካታ ማረጋገጥ ተችሏል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ