53ኛው የሸገር ደርቢ በአዲስ አበባ ስታዲየም

You are currently viewing 53ኛው የሸገር ደርቢ በአዲስ አበባ ስታዲየም

AMN-ጥቅምት 7/2019 ዓ.ም

የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት መርሃግብር የሀገሪቱ ትልቁ ደርቢ ይስተናገድበታል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ኢትዮጵያ ቡና የሚያደርጉት በተለምዶ “የሸገር ደርቢ” በሚል የተሰየመው ፍልሚያ ዛሬ ይከናወናል።

ሁለቱ ክለቦች ካላቸው የገዘፈ ድጋፍ መነሻ በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚከናወነው ጨዋታ የተዋበ ድባብ ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።

መሰረታቸውን አዲስ አበባ ያደረጉት ሁለቱ ክለቦች ለዘንድሮ የውድድር ዓመት ውጤታማ ያደርገናል ብለው ያሰቧቸውን ለውጦች አድርገዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ የቀድሞ ውጤታማ አሰልጣኙ ሰርዲዮቪች ሚሉቲን (ሚቾ) ሾሟል። አምስት የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ በማሸነፍ ጊዮርጊስን የሊጉ ሃያል ክለብ ያደረጉት ሰርቢያዊ አሰልጣኝ በመጀመሪያ ጨዋታቸው ከነጌሌ አርሲ ጋር 1ለ1 ተለያይተዋል። ከ17 ዓመታት በኋላ ተመልሰው ያደረጉት ጨዋታ ምንም እንኳን ነጥብ በመጋራት ቢጠናቀቅም እንቅስቃሴው ደጋፊዎቹን ያስደሰተ ነበር።

ኢትዮጵያ ቡናም የቀድሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ ታሪካዊ ተጫዋች እና የተለያዩ ክለቦችን በማሰልጠን ውጤታማ የሆነው ገብረመድህን ሃይሌን አምጥቷል። ከሦስት የተለያዩ ክለቦች ጋር የሊግ ዋንጫ በማሸነፍ ብቸኛው አሰልጣኝ የሆነው ገብረመድህን ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ቡናን የመምራት ዕድል ነበረው።

ነገር ግን በቡናማዎቹ ቆይታው የፈለገውን ስኬታ አላመጣም። የበለጠ ልምድ ያካበተው እና ስኬት የማያቃቸው ጅማ አባጅፋር ፣ መቐለ 70 እንደርታ እና ኢትዮጵያ መድንን የሊግ ዋንጫ ባለቤት ያደረገው ገብረመድህን ሃይሌ ወደ ኢትዮጵያ ቡና የተመለሰው ተመሳሳዩን እንዲያደርግ ነው። ኢትዮጵያ ቡና በመጀመሪያ ጨዋታው በሸገር ከተማ 1ለ0 ተሰንፎ ቢጀምርም ቡድኑ በደጋፊዎች ተወድሷል።

የመዲናይቱ ድምቀት የሆነው የደርቢ ጨዋታ 9፡00 ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይከናወናል። ሁለቱ ክለቦች ከዚህ ቀደም ለ52 ጊዜ ተገናኝተው ጊዮርጊስ 22ቱን በማሸነፍ የበላይነቱን ሲወስድ ፣ ኢትዮጵያ ቡና 10 ጊዜ ድል አጣጥሟል። 20 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። ለመጨረሻ ጊዜ በተገናኙበት ያለፈው ዓመት ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና 3ለ1 ማሸነፉ ይታወሳል።

53ኛው ደርቢስ በማን አሸናፊነት ይጠናቀቃል?

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review