AMN- ጥቅምት 30/2017 ዓ.ም
እየተገነባ የሚገኘው የመከላከያ ኃይል ለሀገር ሉዓላዊነት እና ብሔራዊ ጥቅሞች መረጋገጥ ዋስትና ነው ሲሉ የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬዳዋን ሁሴን ገለጹ፡፡
አምባሳደር ሬድዋን ከመከላከያ አዛዥነትእና ስታፍ ኮሌጅ ተማሪዎች አመራሮች እና መምህራን ጋር በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ባደረጉት ውይይት ከሁሉም ሀገራት ጋር ሰላምን እና ብሔራዊ ጥቅምን ያስቀደመ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ አውስተው ይህንኑ አጠናክሮ በማስቀጠል ኢትዮጵያ በአህጉራዊ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ያላትን ተሰሚነት አስጠብቆ ማስኬድ ተችሏል ብለዋል።
የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች ማዕከል ያደረጉ የደህንነት እና የዲፕሎማሲ ስራዎች በመሰረታቸው ስኬታማ ውጤት ሊመዘገብ መቻሉንም አስረድተዋል፡፡
አምባሳደር ሬድዋን ኢትዮጵያ ከፍተኛ ስትራቴጂክ ጠቀሜታ ባለው የአፍሪካ ቀንድ እንደመገኘቷ፣ በአህጉራዊና ዓለም አቀፍ ብዝኻ ተዋንያን መድረኮች መስራችና ንቁ ተሳታፊነቷ ጎረቤት ሀገራትን በማስቀደም አጋርነትን በማስፋት ፣ በኢኮኖሚ ፣ በማህበራዊ እና በደህንነት ጉዳዮች ዙርያ በትብብር መስራት የሚያስችል ፖሊሲ ተቀርጾ እየተሰራበት እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የውስጥ ሰላምና አንድነት፣የሰከነ ማህበራዊና ፖለቲካዊ መስተጋብር ዋናው የጥንካሬ ምንጭ ነው ያሉት አምባሳደር ሬድዋን ይህንንም ለማረጋገጥ ብሄራዊ መግባባትን ማጉልበት፣ ድህነትን መቅረፍና አካታችና ፍትሃዊ እድገት ማረጋገጥ፣ እየተለወጠ የመጣውን ዓለማዊ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ ወትሮ ዝግጁነት እውን ማድረግ እንደሚገባ ገልፀዋል።
ይህንኑ ግምት ውስጥ ያስገባ የአስር ዓመት መሪ እቅድ መዘጋጀቱን ፣ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መቀረፁንና ለመጀመሪያ ጊዜ ራሱን የቻለ የብሄራዊ ደህነት ፖሊሲ ቀረፃም በመጠናቀቅ ላይ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ያለ ጠንካራ የመከላከያ ሠራዊትና የደህንነት ተቋማት አስተማማኝ ሰላም ማስፈንና ብሄራዊ ጥቅምን መከላከል አዳጋች ነው ያሉት አምባሳደር ሬድዋን ኢትየጵያን በሚመጥን ልክ እየተገነባ የሚገኘው የመከላከያ ኃይል ለሀገራን ሉዓላዊነት እና በሔራዊ ጥቅሞች መረጋገጥ ዋስትና ነው ሲሉ ገልጸዋል።
በምግብ ሰብል ራስን ከመቻል ጀምሮ በሁሉም ዘርፍ የህዝቦችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና ውስጣዊ አንድነትን ለማጠናከር መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
የመከላከያ አዛዥነትእና ስታፍ ኮሌጅ አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል ሙሉጌታ አምባቸው በበኩላቸው የመከላከያ አዛዥነት እና ስታፍ ኮሌጅ የመከላከያ ሰራዊታችንን ወታደራዊ አመራሮች አቅም ለማሳደግ በአጭር እና በረዥም ኮርስ መርሃ ግብሮች ተከታታይነት ያላቸው ስልጠናዎች እየተሰጡ እንደሚገኙ አውስተው ስልጠናዎቹ በመከላከያ ሰራዊታችን ሁለንተናዊ የማድረግ አቅም ላይ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ገልጸዋል ።
ብርጋዲየር ጄኔራል ሙሉጌታ አምባቸው የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በመከላከያ አዛዥነት እና ስታፍ ኮሌጅ ተገኝተው ለሰጡት ሀገራዊ እና ወቅታዊ ገለጻ በማመስገን የኮሌጁን አርማ በስጦታ ማበርከታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት የማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።