ለአቶ በላይ ደጀን የአፍሪካ ወጣት መሪዎች ኮንፍረንስ ላይ እውቅና ተሰጣቸው

You are currently viewing ለአቶ በላይ ደጀን የአፍሪካ ወጣት መሪዎች ኮንፍረንስ ላይ እውቅና ተሰጣቸው

AMN – የካቲት 17/2017 ዓ.ም

“የፓን አፍሪካኒዝም አዲስ መንፈስ በግሎባላይዜሽን፣በኢኖቬሽን መር የኢኮኖሚ ውህደት ለሰላም ግንባታ” በሚል መሪ ሐሳብ እየተካሄደ በሚገኘው የአፍሪካ ወጣት መሪዎች ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ኮንፈረንስ ላይ ለአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፓርት ቢሮ ኃላፊ ለአቶ በላይ ደጀን ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እውቅና ተሰጣቸው፡፡

በኮንፈረንሱ ላይ የቀድሞ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬን ጨምሮ የፌዴራል እና የከተማ አስተዳሩ ከፍተኛ አመራሮች፣ ዲፕሎማቶች እና የአለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች እንዲሁም ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት፣ ዩኒቨርስቲዎችና ከሲቪክ ማህበራት የተውጣጡ ከ300 በላይ ወጣት መሪዎች ተሳትፈዋል፡፡

የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ወጣቶች ውይይት ለሰላም ማህበር እና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በተሰናዳው ዝግጅት ላይ የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፓርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በላይ ደጀን ስፓርትን ለዘላቂ ሰላም ግንባታ በመጠቀም ላደረጉት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እውቅና ተችሯቸዋል፡፡

ያለ ሰላም ጠንካራ ኢኮኖሚን መገንባትና ዘላቂ ዕድገትን ማረጋገጥ አዳጋች ነው ያሉት የቀድሞ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሐይለማሪያም ደሳለኝ ወጣቶች ችግሮችን በውይይት የመፍታት ልምድ ሊያዳብሩ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው የአፍሪካን አንድነት ለማረጋገጥ ወጣቶች ያላቸውን እምቅ አቅም በመጠቀም አፍሪካን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር ይገባል ብለዋል።

የአፍሪካ ታላላቅ መሪዎች ለዓለም የነበራቸውን አበርክቶ በንግግሩ ያወሳው የኢትዮጵያ ወጣቶች ውይይት ለሰላም ማህበር ዳይሬክተር ኢንጂነር ጫላ፣ ኮንፈረንሱ ወጣት አመራሮች ስለዲፕሎማሲ እና ስለ ዓለም አቀፍ ግንኙነት የሚመክሩበት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በኮንፍረንሱ ላይ የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ አቀንቃኙ ፕሮፌሰር ፓትሪስ ሉሙቧ፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሹሩን አለማየሁ (ዶ/ር)፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የወጣቶች እና ስፖርት አማካሪ ሚኒስትር አቶ ቀጀላ መርዳሳን ጨምሮ ተጋባዥ እንግዶች መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን የአፍሪካ ወጣቶች ድምጽ ለማሰማት ፍላጎታቸውን ለማሳካት በአንድነት መንፈስ እንዲሰራ ጥሪ መቅረቡን ከአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፓርት ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review