AMN – ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም
የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ፈጠራ የታከለበት መፍትሔን እንደሚሻ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ከረሀብ ነፃ ዓለም” በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው ኮንፈረንስ ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል።
በእንኳ ደህና መጣችሁ መልእክታቸውም ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መገኛ፣ የቡና መገኛ፣ የራሷ የቀን ቀመር እና ፊደል ያላት ምድረ ቀደምት መሆኗን ለኮንፈረንሱ ታዳሚዎች አስታውቀዋል። ኮንፍረንሱን ላዘጋጁ አካላትም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ዓለምን ከረሀብ ነፃ ለማድረግ በምናደርገው ጥረት የአየር ንብረት ለውጥ፣ በዓለም ዙሪያ ያሉ ግጭቶች፣ የተፈጥሮ አደጋዎች እና ኮቪድ-19 የተፈታተኑን ቢሆንም ከዚህ ወርቃማ ዓላማችን ሊያቆሙን አልቻሉም፤ ይልቁን ጥረታችንን በእጥፍ እንድንጨመር አደረጉን እንጂ ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ።
አክለውም፣ አሁን ባለው የዓለም ቀውስ እና እየጨመረ ከመጣው የሕዝበ ቁጥር ጋር የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ፈጠራ ታከለበት መፍትሔን የሚሻ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።
በመሆኑም ያልተቋረጠ ጥረት፣ ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴን ማሳደግ፣ ወሳኝ የግብርና ግብዓቶችን ማስፋት እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥን በመቆጣጠር ምርታማነትን መጨመር እንደሚገባ አብራርተዋል።
ዓለምን ከረሀብ ነፃ ማውጣት ምርታማነትን ከመጨመርም ያለፈ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ድህነትን፣ ኢ-ፍትሐዊነት እና የአየር ንብረት ለውጥ ችግሮችንም በሁለንተናዊ መልኩ መፍታትን ይጠይቃል በለዋል።
ኢትዮጵያ ለሁሉም ዜጎቿ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ አመርቂ ተግባራትን እያከናወነች እንደምትገንም ተናግረዋል።
በማሬ ቃጦ