የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአፍሪካ ከፍተኛ አማካሪ ማሳድ ቦሎስ ጋር ተወያይተዋል።
ውይይቱ የተካሔደው በአንጎላ ርዕሰ መዲና እየተካሄደ ካለው የአፍሪካ አሜሪካ የቢዝነስ ጉባኤ ጎን ለጎን ነው።
በውይይቱም ለበርካታ ዓመታት የዘለቀውን የሁለቱን አገራት ታሪካዊ ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ዘሪያ መምከራቸውን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓና የአሜሪካ ጉዳዮች ምክትል ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ሙሌ ታረቀኝ ገልጸዋል።
በተለይም አሁን ላይ አሜሪካ ለአፍሪካ አገራት ትኩረት በሰጠችው የኢንቨስትመንትና የንግድ ዲፕሎማሲ ማዕቀፍ ሁለቱ አገራት በዘርፉ ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማሳደግና ለማስፋት ከመግባባት ላይ መድረሳቸውንም ጠቁመዋል።
በሌላ በኩልም በቀጣናዊ የልማትና የሠላም ጉዳዮች ዙሪያ መምክራቸውን አምባሳደር ሙሌ በስፍራው ለሚገኘው የኢዜአ ሪፖርተር ገልጸዋል።