ህዝቡ በአጭር መልዕክት አሻራውን ለታሪክ መዘክርነት እንዲያስቀምጥ ያለመ መርሃ ግብር ይፋ ሆኗል፡፡
የታላቁ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቁን ተከትሎ በግንባታው ላይ ሲረባረቡ የቆዩ ኢትዮጵያዊያን፤ ደስታቸውን፣ ስሜታቸውና እና የድል ብስራታቸውን የሚያጋሩበት “የአጭር መልዕክት ማስተላለፊያ ኮድ፦ 8120” ይፋ ተደርጓል።
በታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ይፋ የተደረገውና “የትውልድ አሻራ ዲጂታል የብስራት መልዕክትና ገቢ ማስገኛ ፕሮጀክት” የሚል ስያሜ የያዘው ፕሮጀክት ከዛሬ ነሐሴ 27 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ እስከ መስከረም 30 ቀን 2018 ዓ.ም የሚቆይ እንደሆነ ተገልጿል።
ፕሮጀክቱ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ለእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ምን ማለት ነው? የሚለውን ጥያቄ ግለሰቦች ያሰላሰሉትን እና በአዕምሯቸው የሚመጣውን ሃሳብና መልዕክት ስልካቸውን በመጠቀም ማስተላለፍ እንዲችሉ የሚያደርግም ነው ተብሏል።
የእያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ስሜት፣ ሃሳብና መልዕክት ለታሪክ ከትቦ ማስቀመጥ አንዱ የህዝባዊ ተሳትፎ አካል በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ መልዕክቱን የሚያቀርብበትና ለትውልድ እንዲተላለፍ የትውልድ አሻራ ዲጂታል መልዕክት ፕሮጀክት መቅረጽና መተግበር አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ነው የማስተባበሪያ ጽ/ቤቱ ኃላፊ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) የተናገሩት።
በአጭር መልዕክት ማስተላለፊያው 8120 ላይ፡
1 ቁጥር፡ “በህብረት ችለናል!” መልዕክት ሲጫን – 5 ብር ድጋፍ፤
2 ቁጥር፡ “ህዳሴ ግድብ የብልጽግናችን አሻራ!” መልዕክት ሲጫን – 10 ብር ድጋፍ፤
3 ቁጥር፡ “ግድባችን፤ የአሸናፊነት ድል አክሊል!” መልዕክት ሲጫን – 15 ብር ድጋፍ፤
4 ቁጥር፡ “ግድባችን፤ የአባይ ዘመን ትውልድ የተጋድሎ ሰንደቅ!” መልዕክት ሲጫን – 100 ብር ድጋፍ፤
ወይም የራስዎን መልዕክት ሲልኩ በ20 ብር ድጋፍ ማድረግ እንደሚቻልም ተገልጿል።
በበላይሁን ፍሰሀ