የ2018 የኢሬቻ በዓል ባህልና ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ በድምቀት ተከብሮ መጠናቀቁን አባ ገዳ ጎበና ሆላ ተናገሩ

You are currently viewing የ2018 የኢሬቻ በዓል ባህልና ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ በድምቀት ተከብሮ መጠናቀቁን አባ ገዳ ጎበና ሆላ ተናገሩ

AMN-መስከረም 25/2018 ዓ.ም

የኢሬቻ በዓል የኦሮሞ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ብሔር ብሔረሰቦች በተገኙበት በድምቀት መከበሩን ነው አባ ገዳ ጎበና በሰጡት መግለጫ የተናገሩት።

ኢሬቻ የገዳ ስርዓት መገለጫ እና የኦሮሞ ህዝብ የባህል ሀብት ነው ያሉት አባ ገዳ ጎበና ያለ ሀይማኖት እና ሌሎች ልዩነቶች በድምቀት ተከብሮ መጠናቀቁን ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ የተሰራው የልማት ስራ የሆረ ፊንፊኔ ኢሬቻ በድምቀት እና በተለየ ሁኔታ እንዲከበር አስችሎታል ያሉት አባ ገዳ ጎበና የቢሾፍቱ ከተማም ቢሆን በከፍተኛ ደረጃ አምራ እና ደምቃ በዓሉ እንዲከበር አድርጋለች ነው ያሉት።

ከእንግዶች አቀባበል ጀምሮ በዓሉ በድምቀት እና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላትም ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።

የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ጀሚላ ሲንብሩ በበኩላቸው የ2018 የኢሬቻ በዓል የኢሬቻ ማክበሪያ ስፍራዎችን ታሪካቸውን እና የህዝቡን ክብር በሚመጥን መልኩ ጸድተው እና ለምተው መከበሩ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።

በሚሊዮኖች የሚቆጠር ህዝብ፣ በሀይማኖት ፣ በፖለቲካ ልዩነት እና በሌሎችም መስኮች ሳይለያይ ባህልና ወጉን በጠበቀ መልኩ በዓሉን አክብሯል ያሉት ኃላፊዋ ኢሬቻ የፍቅር እና የሰላም በዓል መሆኑም በተጨባጭ የታየበት ነው ብለዋል።

በኢሬቻ በዓል የሚታየው የባህል አልባሳት ድምቀት እና የባህል ኢንዱስትሪ እድገት የስራ እድል ከመፍጠር ባሻገር ለቱሪዝም ስህበት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን ያነሱት ወይዘሮ ጀሚላ በዘንድሮው ኢሬቻም ከተለያዩ ሀገራት የተወጣጡ ጎብኚዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

በዓሉ እሴቱን ጠብቆ በድምቀት እንዲከበር አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።

በሰብስቤ ባዩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review