የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ እና ለምስራቅ አፍሪካ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ አበርክቶ እንደሚኖረው የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሀመድ ተናገሩ

You are currently viewing የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ እና ለምስራቅ አፍሪካ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ አበርክቶ እንደሚኖረው የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሀመድ ተናገሩ

AMN መስከረም 28/2018

የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ እና ለምስራቅ አፍሪካ የሚኖረው ኢኮኖሚያዊ አበርክቶ ከፍተኛ እንደሆነ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሀመድ ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንቱ በሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት ባለቤትነት ከሚተዳደረው ከአል-ዓረቢያ የዜና ጣብያ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ግድቡ በተፋሰሱ ሀገራት ላይ ጉዳት ያስከትላል የሚል እምነት እንደሌላቸው ገልጸዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከአሥር ዓመት በላይ ግንባታ ላይ የቆየ ትልቅ ፕሮጀክት እንደሆነ የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ የተገነባውም ኃይል ለማመንጨት ነው ብለዋል።

ከ5,000 ሜጋ ዋት በላይ ኃይል የሚያመነጨው ግድብ በእርግጠኝነት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንዲሁም በቀጠናው ላይ በጎ ተጽዕኖ እንደሚኖረው አብራርተዋል።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ለኬንያ፣ ለሱዳን፣ ለጅቡቲ የኤሌክትሪክ ኃይል እያቀረበች እንደምትገኝ አንስተው ፤ ኃይል እና ኤሌክትሪክ ለማንኛውም ልማት በጣም አስፈላጊ ነገር ነው ብለዋል።

ሌሎች ጉዳዮች ሊኖሩ ይችላሉ ፣ ነገር ግን ግድቡ በራሱ በኢትዮጵያ ህዝብ እና በኢትዮጵያ መንግስት በተሳካ ሁኔታ የተገነባ መሆኑ ትልቅ ስኬት እንደሆነም ነው የጠቆሙት ።

ፕሬዚዳንቱ ሶማሊያ ከግብፅ ጋር ስትራቴጂካዊ አጋርነት መፈራረሟን እና ከኢትዮጵያ ጋር ሀገራቸው ስላላት ግንኙነት ተጠይቀው ነበር።

በምላሻቸውም “ኢትዮጵያ የሶማሊያ ጎረቤት ከመሆን ባሻገር የአፍሪካ ህብረት ተልዕኮ አካል ነች፣ ወደ 2,000 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ድንበር እንጋራለን፣ በድንበሩ በሁለቱም በኩል ያለው ህዝብ አንድ ነው ሌሎች የጋራ የሚያደርጉን ብዙ ጉዳዮችም አሉ” ሲሉ ተናግረዋል ።

አክለውም “ከኢትዮጵያ ጋር ያለን ግንኙነት ከግብፅ ጋር ያለንን ስትራቴጂያዊ ግንኙነት ለመጉዳት የታለመ አይደለም” ብለዋል።

በግድቡ እና በአባይ ውሀ አጠቃቀም ዙሪያ ኢትዮጵያ እና ግብፅ ልዩነቶቻቸውን የሚፈቱበት ሰፊ እድል እንዳለ የጠቆሙት ፕሬዝዳንቱ መንግስታቸው ይህን ሂደት ለማገዝ ዝግጁ መሆኑን አመላክተዋል።

በዳዊት በሪሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review