ቅዱስ ጊዮርጊስ የአዲስ አበባ ከተማ ህዳሴ ዋንጫ አሸናፊ ሆነ

You are currently viewing ቅዱስ ጊዮርጊስ የአዲስ አበባ ከተማ ህዳሴ ዋንጫ አሸናፊ ሆነ

AMN-ጥቅምት 02/2018 ዓ.ም

የ19ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ህዳሴ ዋንጫ በቅዱስ ጊዮርጊስ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስን እና መቻልን ያገናኘው የፍፃሜ ጨዋታ በጊዮርጊስ 2ለ1 አሸናፊነት መጠናቀቅ ችሏል።

በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ለቅዱስ ጊዮርጊስ አሸናፊ ጌታቸው እና አዲሱ አቱላ የማሸነፊያ ግቦቹን ከመረብ አሳርፈዋል።

የመቻልን ብቸኛ ግብ የቅዱስ ጊዮርጊሱ ተከላካይ ሄኖክ ዮሐንስ በራሱ ላይ አስቆጥሯል።

በጨዋታው በመቻል በኩል ግሩም ሀጎስ በሁለት ቢጫ ተማም ሀቢብ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥተዋል።

የጨዋታውን የማሸነፊያ ግብ ያስቆጠረው አዲሱ አቱላ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ ተመርጧል።

19ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ህዳሴ ዋንጫ በቅዱስ ጊዮርጊስ አሸናፊነት ሲጠናቀቅ መቻል እና ኢትዮጵያ ቡና ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል።

በዛሬው መርሃ ግብር የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ መኪዩ ሞሐመድ ፣ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ፣ የአዲስ አበባ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ሃላፊን ጨምሮ ሌሎች ሃላፊዎች በክብር እንግድነት ተገኝተው ለአሸናፊዎች ሽልማት አበርክተዋል።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review