AMN – ጥቅምት 05/2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ ከ100 አመታት በላይ የተሻገረ ታሪክ ያላት ከተማ ናት ።
እንደ ዕድሜዋ እና ዓለም ዓቀፍ ከተማነቷ በቂ የሚባል የኪነ-ጥበብ መሰረተ ልማት አልነበራትም ፡፡
መዲናዋ ከቅርብ አመታት ወዲህ የለፉ አመታት የቤት ስራዋን ለመከወን ዘመናዊ ከተማ ሊያሟላ የሚገባውን የኪነ-ጥበብ መሰረተ ልማቶች እያሟላች ትገኛለች ። በዘመናት ያልተገነቡ ግዙፍ ሲኒማ ቤቶች ተገንብተው ለተደራሲያኑ ማቅረብ ተችሏል፡፡
በከተማዋ አሁን ላይ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ይህም ከሚገለጥበት ወይም ከሚታይበት መካከል አንዱ ለኪነ-ጥበብ የምትሰጠው ቦታ ነው ። በአዲስ አበባ የቲያትር እና ሲኒማ ቤቶች መከፈት ከሁለተኛው በጣሊያን ወረራ ግዜ በኋላ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል። ይሁን እንጂ ካስቆጠረው ዕድሜ አንፃር የዘርፉ ዕድገት እንደ ግመል ሽንት ወደ ኋላ የቀረ ነበር ፡፡ ለዚህ ማሳያ የሆኑ ዘመናትን የተሻገሩት ቴአትር ቤቶችና የኪነ-ጥበብ ማዕከላትም ህያው ምስክሮች ሆነው ዘልቀዋል።
ነገር ግን አዲስ አበባ ያላትን አስደናቂ የተፈጥሮ፣ የታሪክና የማህበረሰብ አወቃቀር በሚመጥን ልክ የኪነ-ጥበብ ዘርፉ እንዳላደገ በርካቶች ይስማማሉ። ለበርካታ ዘመናት ከከተማዋ እድገት ጋር የሚጣጣም የኪነ-ጥበብ ማዘውተሪያ ስፍራዎችን የማስፋፋት ስራ በሚፈለገው ልክ አለመከናወኑ ደግሞ የበርካቶች ጥያቄ ሆኖ ቆይቷል።
ታዲያ አሁን ላይ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ አዲስ አበባ ከተማን ለመለወጥ በተከናወኑ የመሰረተ ልማት ስራዎች የመዲናዋን ገጽታ ከመቀየር ባሻገር ለኪነ-ጥበብ ዘርፍ ልዩ ትኩረት የሰጡ ሆነዋል።
በተሰሩ የልማት ስራዎች በርካታ አምፊ ቴአትሮች፣ ሰፊ ህዝብን መያዝ የሚችሉ ፓርኮች እንዲሁም የአርት ጋለሪ ጭምር ያካተቱ መሆናቸው ከበቂ በላይ ማሳያ ናቸው ።
በቅርቡ ተገንብተው የተመረቁት የኪነ-ጥበብ ማዕከላት፣ ዓለም አቀፍ ደረጃን ያሟሉና የሀገራችንን የጥበብ ስራዎች ደረጃ ፣ ከፍ የማድረግ አቅም ያለው ነው ።
ለአመታት በመንግስት ደረጃ ዘመኑን የዋጁ ቲያትር እና ሲኒማ ቤቶች ሳይገነቡ በመቅረታቸው በጥበብ ባለሞያዎች ዘንድ ቅሬታ የፈጠረ ቢሆንም ፣ በ2018 አዲስ አመት ሁለት ትላልቅ ትያትር እና ሲኒማ ቤቶች እንዲሁም ሌሎችም የጥበብ ስራዎችን መከወን የሚያስችሉ መሆናቸውን የተመሰከረላቸው ናቸው ።
ተመርቀው ስራ የጀመሩት የህፃናት እና ወጣቶች ትያትር ቤት እና የአዲስ ሲኒማ ኮምፕሌክስ ለሙያተኞች ጠቀሜታው ላቅ ያለ መሆኑን ተገልጿል ። ታዲያ በሀገራችን ከሚገኙ የኪነ-ጥበብ ባለሞያዎች አንዱ የሆነው የፊልም እና ተውኔት ደራሲና ዳይሬክተር አርቲስት ተሻለ ወርቁ በዚህ ጉዳይ ላይ ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል ሃሳቡን አጋርቶናል ፡፡

ላለፉት በርካታ አስርት ዓመታት በመንግስት ደረጃ የትያትርም ሆነ ሲኒማ ቤት ግንባታ ተከናውኖ እንደማይታወቅ ገልጾ። የዚህ አይነቱ እንቅስቃሴ ከመንግስት ይልቅ በግሉ ሴክተር ብቻ እንደነበር እና የሚይዙት የተመልካች ቁጥር ከ300 እንደማይበልጥ ነው ያወጋን ።
አሁን ላይ ግን እነዚህ ችግሮች በከተማ አስተዳደሩ መፈታታቸው እና የኮምፕሌክሱ ህንፃዎች ለኪነ-ጥበብ ዘርፉ እና ለባለሞያው እንዲሁም ለተመልካች አዲስ ዕይታና እና ጥሩ ዕድል ይዘው መምጣታቸውን ተሻለ ወርቁ ያጫወተን ።
አዲስ ሲኒማ ኮምፕሌክስ እና የህፃናት እና ወጣቶች ቲያትር ሰው የማስተናገድ አቅማቸው ከፍተኛ መሆኑን ነው አርቲስት ተሻለ የገለፀው ፣ ከምንም በላይ በመንግስት በመንገባቱ እንደ ባለሙያ ያለብንን እጥረት የቀረፈና ለስራ የሚያነሳሳ በመሆኑ በጣም ደስተኞች ነን ሲል ነው የተናገረው ።
ሁለቱ የተገነቡት ህንፃዎች ዘመኑን የዋጁ እና በተለይም ወደ ዘርፉ የሚገቡ ጀማሪ ተዋንያን እና ዳሬክተሮችን ለስራ የሚያነሳሳ መሆኑንም የገለፀው ተሻለ ወርቁ እንደ ባለሞያ ከኛ የሚጠበቀው ለተመልካች የሚመጥን ጥራት ያለው የጥበብ ውጤቶችን መስራት ላይ ሊሆን ይገባል ሲል አስተያየቱን አጋርቶናል ።
አቶ ፍፁም ዘገየ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትያትር ቤቶች አስተዳደር ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ ናቸው ፣ የኪነ-ጥበብ ዘርፉን ለማሳደግ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ገልፀው ፣ በተለይም የባለሞያዎች የዘወትር ጥያቄ የነበረው የማሳያ ቦታዎች ጥያቄ ከፍተኛ ለኪነ-ጥበብ ዘርቨከፍተኛ ተግዳሮት እንደነበር ገልፀው አሁን ላይ በከተማዋ የተገነቡ ኮምፕሌክሶች ዘርፉን አንድ እርምጃ ከፍ እንዲል ያደርጋል ነው ያሉት ።

በለውጡ አመታት የኪነ-ጥበቡን ማህበረሰብ በማቅረብና በማነጋገር ላነሳቸው ችግሮች መፍትሄ በመስጠትና ሙያተኛውን በመረዳት የተቋም ግንባታ መጀመሩ የሚበረታታ ነው ብለዋል ።
የህጻናት እና ወጣቶች ቲያትር ቤቶች እና አዲስ ሲኒማ ኮምፕሌክሶች አዲስ አበባን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጰያን ኪነ-ጥበብ ባለሞያዎች ችግር የቀረፈ ባለሞያውም በሙሉ ዓቅሙ እንዲሰራና ሀገር ከኪነ-ጥበብ ማግኘት ያለባትን ጥቅም ከማስገኘት አኳያ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል ።
እነዚህ ኮምፕሌክሶች በኢትዮጰያ የኪነ-ጥበብ ታሪክ ውስጥ ትልቅ እጥፋት የሆኑ ፕሮጀክቶች መሆናቸውና ፋይዳቸውም በብዙ መንገድ የሚተነተን ነው ሲሉ ነው አቶ ፍፁም የገለፁት።
በከተማ አስተዳደሩ የተመረቁት ሁለቱም ተቋማት ህፃናት እና ታዳጊዎች በአጠቃላይ ትውልድን መሰረት ያደረጉ በመሆናቸው ፋይዳቸው ላቅ ያለ ነው ብለዋል ።
ትውልድን በማስተማር እና ለሃገር ዕድገት መነሳሳትን ለመፍጠር ለሞራል ግንባታ እንዲሁም ወንድማማችነትን ለማጠናከር እና ሀገራዊ ፍቅር ለማፅናት የሚያግዝ መሆኑን ነው አቶ ፍፁም የገለፁት ።
በቀጣይ የሚቀረው ከባለሞያው ጥራት ያላቸው እና ተወዳዳሪ ሃሳብ እና ይዘት በማምጣት የኪነ-ጥበብ ማህበረሰቡን ማገልገልና ለኪነ-ጥበብ ዕድገት የድርሻን መወጣት ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ይገባል ሲሉ ከኤ ኤም ኤን ዲጂታል ጋር በነበራቸው ቆይታ አንስተዋል ፡፡
በሔለን ተስፋዬ