43ኛው የአዲስ አበባ ሀገር አቋራጭ ውድድር ከነገ በስቲያ እንደሚካሄድ የመዲናዋ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡
አትሌቶች ለሀገራዊ ውድድሮች ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ እና ተተኪ አትሌቶችን ማፍራት የውድድሩ ዋነኛ ዓላማ መሆኑን የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚደንት አትሌት መልካሙ ተገኝ ተናግሯል፡፡
ፌዴሬሽኑ ለጃን ሜዳ ለሚካሄደው የሀገር አቋራጭ ውድድር አሸናፊ አትሌቶች በድምሩ ግማሽ ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ሽልማት ማዘጋጀቱን ዛሬ በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ጠቁሟል፡፡
በአንደኛ ዲቪዚዮን 77 ወንዶችና 63 ሴቶች ፣ በሁለተኛ ዲቪዚዮን 156 ወንዶችና 94 ሴቶች እንዲሁም በግል 38 ወንዶችና 4 ሴቶች በድምሩ 488 አትሌቶች በእሁዱ ውድድር እንደሚሳተፉ በመግለጫው ላይ ተነስቷል፡፡
የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር ሆነው የጃን ሜዳ የሀገር አቋራጭ የመሮጫ መስመሩን የማስተካከልና ጥገና ስራ መስራታቸውም በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተጠቁሟል፡፡
በታምራት አበራ