ዶናልድ ትራምፕ ባልተለመደ ሁኔታ በሶስተኛ ዙር የስልጣን ዘመን አሜሪካን ሊያስተዳድሩ እንደሚችሉ ተነገረ

You are currently viewing ዶናልድ ትራምፕ ባልተለመደ ሁኔታ በሶስተኛ ዙር የስልጣን ዘመን አሜሪካን ሊያስተዳድሩ እንደሚችሉ ተነገረ

AMN – ጥቅምት 17/2018 ዓ.ም

አሜሪካን ለሁለተኛ ዙር እያስተዳደሩ የሚገኙት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በ2028 ፕሬዝዳንት ሆነው ሊቀጥሉ እንደሚችሉ የቀድሞ የስትራቴጂ አማካሪያቸው ስቲቭ ባነን ተናግረዋል።

የቀድሞው የኋይት ሀውስ ዋና ስትራቴጂስት ስቲቭ ባነን፤ ከኢኮኖሚስት ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች የስልጣን ዘመን ከሁለት እንዳያልፍ ከሚደነግገው የህገ መንግስት አንቀጽ በተጻራሪ ለሶስተኛ ጊዜ ሀገሪቷን ሊመሩ እንደሚችሉ ነው የተናገሩት።

አሜሪካውያን፤ ትራምፕ ተጨማሪ የማስተዳደሪያ ጊዜ እንዲያገኙ ይፈልጋሉ ያሉት አማካሪው፤ ይህንን ለመቀበል ዝግጁ ያልሆኑ አካላት ራሳቸውን ሊያዘጋጁ ይገባል ብለዋል።

ትራምፕ በ2028 ምርጫ ዳግም ፕሬዝዳንት ሆነው ሊቀጥሉ እንደሚችሉ የተለያዩ ጭምጭምታዎች መሰማት ከጀመሩ ሰንበትበት ብሏል።

የፕሬዝዳንቱ ቀንደኛ ደጋፊዎች፤ ፕሬዝዳንቱ በአሜሪካ እና በአለም አቀፍ ደረጃ ያስጀመሯቸውን ስራዎች ለመጨረስ ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልጋቸዋል እያሉ እንደሚገኙ ሳውዝ ቻይና ሞርኒንግ ፖስት ጽፏል።

ይህ እንዲሆን የሚፈልጉ ደጋፊዎችም ሆኑ ባለስልጣናት አሜሪካ እንደ ዓይኗ ብሌን ከምትጠብቀው ህገ መንግስት በተጻራሪ፤ ትራምፕ በምን አይነት መንገድ ለሶስተኛ ጊዜ ፕሬዝዳንት ሊሆኑ እንደሚችሉ ያሉት ነገር የለም።

የቀድሞው አማካሪ ስቲቭ ባነን በበኩላቸው፤ ይህን ለማድረግ ብዙ መንገዶች እንዳሉ ተናግረው፤ ጉዳዩ የሚፈጸምበት ዕቅድ ጊዜው ሲደርስ ይፋ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል።

በዳዊት በሪሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review