ኦሮሚያ ክልል የሁለተኛው የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሎምፒክ ጨዋታዎች አጠቃላይ አሸናፊ ሆኗል።
ከጥቅምት 15 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው ውድድር ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደ የመዝጊያ ስነ ስርዓት ተጠናቋል።
በመዝጊያው ስነ ስርዓቱ ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የወጣቶች እና ስፖርት አማካሪ ሚኒስትር አቶ ቀጄላ መርዳሳ፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ዶክተር አሸብር ወልደ ጊዮርጊስ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ፣ የብሄራዊ ስፖርት ፌዴሬሽኖች አመራሮች እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።
በሁለተኛው የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሎምፒክ ጨዋታ የኦሮሚያ ክልል 85 ወርቅ፣ 41 ብር፣ 44 ነሀስ በድምሩ 170 ሜዳሊያ በማስመዝገብ አንደኛ ሆኖ አጠናቋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 44 ወርቅ ፣ 48 ብር፣ 37 ነሀስ በድምሩ 129 ሜዳሊያ በማስመዝገብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።
የአማራ ክልል 27 ወርቅ፣ 38 ብር ፣ 36 ነሀስ በድምሩ 101 ሜዳሊያ በማስመዝገብ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።
በዚሁ መሰረት አሸናፊ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የዋንጫ ተሸላሚ መሆን ችለዋል።
በሁለተኛው የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሎምፒክ ጨዋታ ላይ ለተሳተፉ ክልሎችና ከተማ አሰተዳደሮች የተሳትፎ ዋንጫም ተበርክቶላቸዋል።
በኦሎምፒክ ወጣቶች ጨዋታ በ20 የስፖርት አይነቶች ከ5 ሺህ በላይ የስፖርት ልዑካን መሳተፋቸውን የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
የወጣቶች ኦሎምፒክ ውድድር ለሀገር ማንሰራራት” የውድድሩ መሪ ሀሳብ ነው።
የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ የወጣቶች ጨዋታዎች በአዲስ አበባ ስታዲየም እና በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ጨምሮ በተለያዩ ሜዳዎች ሲካሄድ ቆይቷል።
የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ የወጣቶች ጨዋታዎች የተቋረጠውን የወጣቶች ኦሎምፒክ ጨዋታ በማስቀጠል ተተኪ ስፖርተኞችን ለማዘጋጀትና ለማብቃት ዓላማ ማድረጉን የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
የወጣቶች ጨዋታው ለመጀመሪያ ጊዜ በዳካር በሚካሄደው የዓለም የወጣቶች ኦሎምፒክ የሚሳተፉ አትሌቶች የሚመረጡበትም ነው።