ለዓለም አቀፍ የሀገራት ጨዋታዎች ተቋርጦ የነበረው የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ በሚደረጉ ሰባት የ13ኛ ሳምንት መርሃግብር ጨዋታዎች ይመለሳል።
ቀን 9:30 ቼልሲ ከሜዳው ውጪ በተርፍ ሙር በርንሌይን ይገጥማል። ቼልሲ በመጨረሻዎቹ ሁለት የሊግ ጨዋታዎች ቶተንሃም ሆትስፐርስን እና ወልቭስን ማሸነፉ ወደ ሦስተኛ ደረጃ ከፍ አድርጎታል።
በርንሌይ በአንፃሩ በአርሰናል እና ዌስትሃም ዩናይትድ በተከታታይ መሸነፉ ወደ 17ኛ ደረጃ ዝቅ አድርጎታል። በዚህ ጨዋታ ቼልሲ አሁንም ተፅእኖ ፈጣሪው ኮል ፓልመርን ማሰለፍ አይችልም።
ቼልሲ በእርስ በእርስ ግንኙነት በርንሌይ ላይ ያለው የበላይነት የገዘፈ ነው። የምዕራብ ለንደኑ ክለብ በርንሌይን በገጠመበት የመጨረሻ 18 ጨዋታ ሽንፈት የገጠመው በአንዱ ብቻ ነው። 12ቱን አሸንፎ በአምስቱ አቻ ተለያይቷል።
በሌላ ጨዋታ ምሽት 12 ሰዓት ሊቨርፑል ኖቲንግሃም ፎረስትን በአንፊልድ ያስተናግዳል። ሁለቱ ክለቦች ለመጨረሻ ጊዜ በሊጉ ሲገናኙ ሊቨርፑል አንደኛ ፎረስት ደግሞ ሦስተኛ ደረጃ ይዘው ነበር።

ዘንድሮ ሁለቱም ወርደው ሊቨርፑል ስምንተኛ ፎረስት ደግሞ 19ኛ ላይ ተቀምጠው ይገናኛሉ። ባልተጠበቀ መልኩ ውጤት ያጡት ክለቦቹ በዛሬው ጨዋታ ሦስት ነጥቡ በእጅጉ ያስፈልጋቸዋል።
ከመጨረሻዎቹ ስድስት የሊግ ጨዋታ አምስቱን የተሸነፈው ሊቨርፑል በዛሬው ጨዋታ ፍሎሪያን ቨርትዝን አያሰልፍም። ጀርመናዊው አማካይ ለሀገሩ ጀርመን ሲጫወት መጠነኛ ጉዳት ገጥሞታል።
የቀኝ መስመር ተከላካዩ ኮነር ብራድሊም ከስብስቡ ውጪ እንደሆነ ያሳወቁት አርነ ስሎት ግብ ጠባቂው አሊሰን ቤከር ግን ተመልሶላቸዋል። ሾን ዳይችን ከቀጠረ በኋላ የተነቃቃው ፎረስት ባለፈው ዓመት በሊግ ጨዋታ ሊቨርፑልን በአንፊልድ ያሸነፈው ብቸኛ ክለብ ነበር።
በዛሬው ጨዋታም ለሊቨርፑል ፈተና ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል። በተመሳሳይ ምሽት 12 ሰዓት ቦርንማውዝ ከዌስትሃም ዩናይትድ ፣ ብራይተን ከብሬንትፎርድ ፣ ፉልሃም ከሰንደርላንድ እንዲሁም ወልቭስ ከክሪስታል ፓላስ ይጫወታሉ።
ምሽት 2:30 ኒውካስትል ዩናይትድ ማንችስተር ሲቲን ያስተናግዳል። ሊጉ ሀገራት የዓለም አቀፍ ጨዋታ ከመቋረጡ በፊት ሊቨርፑልን የረታው ማንችስተር ሲቲ በዋንጫ ፉክክር ውስጥ መኖሩን አስመስክሯል።
የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ ከመሪው አርሰናል የሚኖረውን የነጥብ ልዩነት አንድ ብቻ ይሆናል። በዛሬው ጨዋታ በትልቁ የሚጠበቀው ኧርሊንግ ሃላንድ ግብ ካስቆጠረ 100ኛው ሆኖ ይመዘገባል።
የ25 ዓመቱ ኖርዌያዊው አጥቂ ከ108 የሊግ ጨዋታ 99 ግቦችን አስቆጥሯል። ሃላንድ ይህን ዛሬ ግብ ማስቆጠር ከቻለ በጥቂት ጨዋታ 100 ግብ ላይ የደረሰ ቀዳሚው ተጫዋች ይሆናል።
ጰዚህ ቀደም አለን ሺረር በ124 ጨዋታ 100 ግብ በማስቆጠር ክብረወሰኑን ይዟል። ከወራጅ ቀጠናው በሁለት ነጥብ ብቻ የራቀው ኒውካስትል ዩናይትድ ከማንችስተር ሲቲ ጋር ያለው የእርስ በእርስ ግንኙነት ውጤት ጥሩ የሚባል አይደለም።
በሊጉ ካደረጋቸው 35 ጨዋታ በ28ቱ በሲቲ ተሸንፏል ፤ ድል የቀናው በአንድ አጋጣሚ ብቻ ነው።
በሸዋንግዛው ግርማ