በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ በኢትዮጵያ የዩናይትድ ኪንግደም አምባሳደር ዳረን ዌልች ጋር ተወያይተዋል።
አቶ አደም በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ እና ዩናይትድ ኪንግደም በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ መስኮች ዘመናትን የተሻገረ ጠንካራ ግንኙነት አላቸው።
ዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ ትልቅ የልማት አጋር መሆኗን ጠቁመው የኢትዮጵያ የልማት እና የሪፎርም አጀንዳ እንዲሳካ ዩናይትድ ኪንግደም ለምትሰጠው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል።
ሀገራቱ በየዘርፉ ያላቸው ጥልቅ ግንኙነት ይበልጥ እንዲጠናከር ብልፅግና ፓርቲ የሚጠበቅበትን ሚና እንደሚያጠናክርም አረጋግጠዋል።
በትምህርት እና በጤና ዘርፍ ያላቸው አጋርነት ውጤታማ መሆኑን ገልጸው፤ ይህ ስኬታማ ትብብር በሌሎች ዘርፎችም ለማስፋት ቁርጠኛ ነን ብለዋል።
በብልፅግና ፓርቲ አመራር ሰጪነት በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ መስኮች ስኬቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰው፤ እነዚህን ስኬቶች ለማስቀጠል የሚደረገው ርብርብ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።
ብልፅግና ፓርቲ ለተቋም ግንባታ ሥራዎች ትኩረት መስጠቱን ጠቁመው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ እና ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንን ጨምሮ ነጻ ገለልተኛ ተቋማት እውን መሆን ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል።
የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ረገድም ፓርቲው ትልልቅ እርምጃዎችን መውሰዱን ገልጸው፤ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት በመንግሥት ካቢኔ እንዲካተቱ መደረጉን ለአብነት አንስተዋል።
ቀጣዩ ምርጫ ፍትሃዊ እና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ጠቁመው፤ ምርጫው የህዝብ ተሳትፎ የተረጋገጠበት ተአማኒ እንዲሆን ብልፅግና ፓርቲ በቁርጠኝነት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
በኢትዮጵያ የዩናይትድ ኪንግደም አምባሳደር እና የአፍሪካ ኀብረት ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ዳረን ዌልች በበኩላቸው ኢትዮጵያ እና ዩናይትድ ኪንግደም ታሪካዊ እና ምሳሌ የሚሆን ግንኙነት ያላቸው መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሪፎርም በትክክለኛ መንገድ ላይ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህም በተሻለ ደረጃ እንደሚቀጥል አምናለሁ ብለዋል።
ዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ የተቋም ግንባታ ሥራዎችን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኗን አምባሳደሩ አረጋግጠዋል።