ኢትዮጵያ ከ17 ዓመት የአፍሪካ ዋንጫ ከ22 ዓመት በኋላ እንድታልፍ ትልቅ አስተዋፆ የነበራቸው ሦስት ተጫዋቾች በይፋ ለሸገር ከተማ ፈርመዋል።
በውድድሩ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የነበረው ዳዊት ካሳው ፣ አምበሉ ቢንያም አብርሃ እና በስነ ስርዓቱ ላይ ያልተገኘው ግብ ጠባቂው ተመስገን ከበደ ናቸው ፊርማቸውን ያኖሩት።
ተጫዋቾቹ በስሪ ፖይንት አካዳሚ የጎለበቱ በመሆናቸው በዛሬው የፊርማ ስነ ስርዓትም የአካዳሚው ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
በሸገር ከተማ በኩልም የክለቡ ፕሬዚዳንት ተወካይ ተገኝተው ተጫዋቾችን ለማስፈረም የፈለጉበትን ምክንያት አብራርተዋል።
ሸገር ከተማ ባለቤትነታቸው ስሪ ፖይንት ከሆኑት ሦስት ተጫዋቾች ውጪ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የሦስተኛ ዓመት አሰልጣኝ ዘላለም መንግስቱንም አስፈርሟል።
ሸገር ከተማ ለስሪ ፖይንት አካዳሚ ለእያንዳንዱ ተጫዋች 500 ሺ ብር ለመክፈል ተስማምቷል።
ተጫዋቾቹም በወር 50 ሺ ብር የሚያስገኝላቸው የሦስት ዓመት ውል ተፈራርመዋል።
በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የፌዴሬሽኑ ዋና ፀሃፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ይህ ፕሮግራም የተዘጋጀው ሌሎች ክለቦች ከአካዳሚ ወይም ከፕሮጀክት ተጫዋች ሲወስዱ በዚህ መልክ ማካካሻ ከፍለው መሆን እንዳለበት ለማሳየት ነው ብለዋል።
ተጫዋቾቹ በቀጣይ የውጪ እድል ካገኙ ክለቡ ለመተባበር ዝግጁ ነውም ተብሏል።
በተሻለ ገንዘብ ዝውውር የሚፈፅሙ ከሆነ ደግሞ ከሸገር ከተማ በተጨማሪ ስሪ ፖይንት እዚህ ላደረሰበት የማካካሻ ገንዘብ እንደሚኖረው ተነግሯል።
ይህ ሂደት ታዳጊዎችን ለማፍራት ለሚጥሩ አሰልጣኞች ፣ ፖሮጀክቶች እና አካዳሚዎች ትልቅ ተነሳሽነት እንደሚፈጥር አቶ ባህሩ ጥላሁን በማጠቃለያ ንግግራቸው ላይ ጠቁመዋል።
በሸዋንግዛው ግርማ