በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተሾሙት ግርማው አበበ (ዶ/ር) ማን ናቸው?

You are currently viewing በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተሾሙት ግርማው አበበ (ዶ/ር) ማን ናቸው?

AMN – የካቲት 01/2018 ዓ.ም

በመንግስታቱ ድርጅት የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ተመራማሪዎች አስተባባሪ ሆነው ግርማው አበበ (ዶ/ር) ተሹመዋል። ለመሆኑ ግርማው አበበ ማን ናቸው?

ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ለመተግበር በምትታትር ሀገር ውስጥ እንደዚህ አይነት በዘርፉ ባለምጡቅ አዕምሮ ኢትዮጵያዊ ማግኝትና በመንግስታቱ ድርጅት ስር የሚገኘውን ዓለም ዓቀፍ ተቋም መምራት የሚኖረው ሚና ቀላል አይደለም ።

ከኒውክለር የጦር መሳሪያ በላይ እጅግ አስፈሪ በሆነው የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ሳይንስ ዘርፍ መሰል ተመራማሪዎችን ማግኝት እንደ ሀገር ቀጣይ ዕጣፋንታችንን የሚወስን ነው።

ኢትዮጵያዊው ሳይንቲስት ግርማው አበበ (ዶ/ር) ይህን የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ወደ መልካም ነገር ለመቀየር በርካታ ምርምሮችን የሠሩ ኢትዮጵያዊ ምሁር ናቸው።

በዓለም ዓቀፉ ግዙፍ የማይክሮሶፍት ኩባንያ ከአውሮፓውያኑ 2023 እስከ አሁን ድረስ (Ai for Good research lab) ግንባር ቀደም ተመራማሪና አሰተባባሪ፣ IBM ሶፍትዌር ኩባንያ ውስጥ ከ3 ዓመት በላይ የተመራማሪዎች አባልና አስተባባሪ፣ በኦክስፎርድ ዩንቨርሲቲ ደግሞ ማሽኖች ለሰው ልጆች ጤና ስለሚያበረክቱበት ጉዳይ መጠነ ሰፊ ምርምር አድርገዋል።

በስታንፎርድ እና በሀርቫርድ ዩንቨርስቲዎች መሠል የሳይንስና ኢንጂነሪንግ የምርምር ሥራዎችን ያከናወኑት ሳይንቲስት ግርማው አበበ 5 ዓለም አቀፍ የሳይንስና ምርምር ጽሑፎችን በግላቸው፣ ከ22 በላይ የሚሆኑትን ደግሞ ከተለያዩ ኩባንያዎችና ስመ ጥር ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመሆን አሳትመዋል ።

ይህ ወጣት ኢትዮጵያዊ ስመ ጥር ሳይንቲስት የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በአውሮፓውያኑ ጥር 26 ቀን 2018 ዓ.ም. ለጠቅላላ ጉባዔው ባቀረቡት ጥቆማ መሠረት ከዓለም ዙሪያ የተመረጡ 40 ታዋቂ የዘርፉ ምሁራን በተውጣጡበትን ፓናል ውስጥ ተካተው ለሦስት ዓመታት እንዲመሩና እንዲያስተባብሩ ተመርጠዋል።

በቀሪ የሥራ ዘመናቸው የሰው ሰራሽ አስተውሎትን (AI) የሰው ልጅ አኗኗር በማቅለልና በማዘመን ረገድ ወሳኝ ሚና እንዲኖረው ለማድረግ ጥናትና ምርምር የሚሠሩ ይሆናል።

በፋሲል ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review