AMN- የካቲት 17/2018 ዓ.ም
የብዙዎችን ቀልብ የገዛው “ዶቢ” የተሰኘው ድመት፣ በተለያዩ ማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን በስፋት እየተጋራ ይገኛል።
በአሜሪካ አላባማ ግዛት የሚገኘው ይህ ድመት፣ ከአራት ጆሮዎች ጋር መወለዱ የብዙዎች መነጋገሪያ ሆኗል።
የ7 ወራት ዕድሜ ያለው ይህ ጥቁር ድመት፣ አራት ጆሮዎች ያለው መሆኑና ጭራውም አጭርና ጥቅልል ያለ መሆኑ ከሌሎች ድመቶች የተለየ እንዲሆን አድርጎታል፡፡
በታዋቂው የ “ሃሪ ፖተር” ፊልም ላይ የሚታወቀውን “ዶቢ” የተሰኘውን ገጸ-ባህሪ ስለሚመስልም ስሙ ተሰጥቶታል።
ጊዜያዊ አሳዳጊው ስቴፋኒ ብራውን እንደገለጸችው፣ ዶቢ እጅግ ተጫዋችና ተግባቢ ድመት ነው።
ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ፣ የዶቢ ሁኔታ “ኦሪኩላር ፖሊዮቲያ” በመባል ይታወቃል።
ይህ ሁኔታ ለየት ያለ የዘረመል ለውጥ ውጤት ሲሆን፣ የሚገርመው ግን እነዚህ ተጨማሪ ጆሮዎች በድመቱ የመስማት ችሎታ ላይ ምንም ዓይነት ችግር አለማስከተላቸው ነው።
በአሁኑ ወቅት ዶቢን በቋሚነት ለማሳደግ የፈለጉ በርካታ ሰዎች ጥያቄ እያቀረቡ ይገኛሉ።
ሆኖም ግን ድመቱ ለቋሚ አሳዳጊዎች ከመሰጠቱ በፊት፤ አስፈላጊው የህክምና ክትትልና ምርመራ፣ ጤንነቱ ሙሉ በሙሉ መረጋገጡን መፈተሸ እና በመጨረሻም ምቹ ወደሆነ ቋሚ መኖሪያው እንደሚሸኝ ኦዲቲ ሴንትራል አስነብቧል፡፡
በአስማረ መኮንን