AMN- መጋቢት 02/2018 ዓ.ም
የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ዙር ዛሬም ቀጥሎ አራት ጨዋታዎች ይከናወናሉ። ምሽት 5 ሰዓት ማንችስተር ሲቲ ወደ ሳንቲያጎ ቤርናቢዩ አቅንቶ ሪያል ማድሪድን የሚገጥምበት ጨዋታ ትልቅ ትኩረት አግኝቷል።
በቅርብ ዓመታት በተደጋጋሚ እየተገናኙ የሚገኙት ሁለቱ ክለቦች የዛሬ ፍልሚያቸው ለ16ኛ ጊዜ ይሆናል።
ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው 15 የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታዎች ተመሳሳይ ውጤት አስመዝገበዋል። ሁለቱም አምስት አምስት ጊዜ ሲያሸንፉ ፣ አምስት ጊዜ አቻ ተለያይተዋል።
በዛሬው ጨዋታ በአልቫሮ አርቤሎዋ የሚመራው ማድሪድ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ያልተሰለፈው ኪሊያን ምባፔ ወደ ልምምድ ቢመለስም መግባቱ አልተረጋገጠም።
ፈረንሳዊ አጥቂ በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ከሌሎች ክለቦች በበለጠ ማንችስተር ሲቲ ላይ በርካታ ግብ አስቆጥሯል። ምባፔ የእንግሊዙ ክለብ ላይ ሰባት ግቦችን አስመዝግቧል።
ጨዋታው ለሲቲው አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ታሪካዊ ይሆናል። የቀድሞ የባርሰሎና እና ባየርን ሙኒክ አሰልጣኝ በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ 190ኛ ጨዋታውን ይመራል። ይህም ከሰር አሌክስ ፈርጉሰን ጋር ታሪክ እንዲጋራ ያደርገዋል።
ስፔናዊው አሰልጣኝ የሚበለጠው 218 ጨዋታ በመሩት ካርሎ አንቸሎቲ ብቻ ነው። ፓሪሰን ዠርማ ከ ቼልሲ የሚያደርጉት ጨዋታ ሌላው የምሽቱ ተጠባቂ ፍልሚያ ነው።
ሁለቱ ክለቦች ለመጨረሻ ጊዜ በተገናኙበት የዓለም የክለቦች ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ ቼልሲ 3ለ0 ማሸነፉ ይታወሳል።

ሁለቱ ክለቦች በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ሲገናኙ ግን ከ10 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። በውድድሩ በተገናኙባቸው አጠቃላይ ስምንት ጨዋታዎች ፒ ኤስ ጂ ሦስቱን ሲያሸንፍ ፣ ቼልሲ ሁለቱን ድል አድርጓል።
በፓርክ ደ ፕሪንስ የሚደረገው የምሽቱ ጨዋታ 5 ሰዓት ላይ ይጀምራል። በተመሳሳይ ሰዓት የዘንድሮ አስገራሚ ቡድን የኖርዌው ቦዶ ግሊምት በሜዳው ስፖርቲንግ ሊዝበንን ያስተናግዳል።
ከሦስቱ ጨዋታዎች ቀደም ብሎ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ መሪው አርሰናል ወደ ጀርመን አቅንቶ ከባየር ሊቨርኩሰን ጋር ይጫወታል።
ሁለቱ ክለቦች በቻምፒየንስ ሊጉ ከ24 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ይገናኛሉ። ከዚህ ቀደም ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች አርሰናል አንዱን አሸንፎ በሌላኛው ነጥብ ተጋርቷል።
በባይ አሬና ምሽት 2:45 በሚጀምረው ጨዋታ የመድፈኞቹ አጥቂ ካይ ሃቨርትዝ የልጅነት ክለቡን በተቃራኒ ይገጥማል።
በሸዋንግዛው ግርማ