ከትናንት እስከ ዛሬ የዘለቀው የኢትዮጵያ ወታደር ድልና ጀግንነት

AMN- ጥቅምት 1/2019 ዓ.ም

ለኢትዮጵያ ወታደር ጀግንነት በደም የተጻፈ ማንነት፣ ድል ደግሞ መታወቂያው ነው፡፡ ከዓድዋ እስከ ካራማራ፣ ከኮሪያ እስከ ሶማሊያ በጽናት ያለፈው ይህ ታሪካዊ ውርስ ፣ ዛሬ ላይ ከዘመናዊ ወታደራዊ ስልጠናና ቴክኖሎጂ ጋር ተዋህዶ የሀገርን ህልውና አስተማማኝ በሆነ ሁኔታ ማስከበሩን ቀጥሏል።

የሀገር ህልውና መሰረት ከሆኑት አምዶች አንዱ የሀገር መከላከያ እና የወታደሩ ጽናት ነው። በኢትዮጵያ የታሪክ ሂደት ውስጥ የወታደሩ ሚና ሀገርን ከውጭ ወራሪዎች እና ከውስጥ አደጋዎች ከመጠበቅ ባለፈ፣ የብሔራዊ ኩራት እና የጀግንነት ምልክት ሆኖ ቀጥሏል።

በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ድል ድንገተኛ አጋጣሚ ሳይሆን የወታደሩ ሁለንተናዊ መታወቂያ ነው።

ወታደሩ ዓላማው ሀገርን ማዳንና ማሸነፍ እንጂ ሽንፈትን ማስተናገድ አለመሆኑ በውስጡ የታነጸ ጽኑ እምነት ነው።

በኢትዮጵያውያን ዘንድ ሀገርን መውደድ እና ለሀገር መስዋዕት መሆን እሴት በደምና በአጥንት ተቀርጾ በትውልድ ቅብብሎሽ ሲሸጋገር ኖሯል።

አባቶችና እናቶች ሀገርን ነጻ አድርገው ያስረከቡበት ታሪካዊ ገድል ለቀጣዩ ትውልድ ትልቅ የኃላፊነት ውርስ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።

ምንም እንኳ ጀግንነት እና ድል ከባህልና ታሪክ የሚቀዳ ቢሆንም፣ በዘመናዊው ዓለም ይህንን ጥንታዊ የጀግንነት ውርስ ከዘመናዊ ወታደራዊ ስልጠና፣ ቴክኖሎጂ እና ስትራቴጂ ጋር ማዋሃድ አስፈላጊ ነው።

ታሪካዊው ጀግንነት ከዘመናዊ እውቀት ጋር ሲጣመር ሀገርን ከማንኛውም ዓይነት የደህንነት ስጋት የመጠበቅ አቅሙ ሙሉ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ወታደር ጀግንነትም ከሀገራዊ ማንነት ጋር የተጋመደና በዘመናዊ ስልጠና የዳበረ ነው።

ይህ በደም የተጻፈና ከአያት ቅድመ አያት የተወረሰ የድል ስነ-ልቦና ኢትዮጵያ ለዘመናት ነጻነቷን እና ክብሯን ጠብቃ እንድትኖር ያስቻላት ዋናው የጥንካሬዋ ምስጢር ሲሆን ፣ አሁን በስልጠና እና በቴክኖሎጂ የተገነባው ዘመናዊ አቅም ደግሞ ኢትዮጵያን የማትደረፈር ፣ ለሞከሯትም ብርቱ ክንዷየሚደቁስ ተከባሪ ሀገር አድርጓታል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review