AMN ጥቅምት 03/2019
ህገወጡ የህወሃት ቡድን በኢትዮጵያ ላይ ከፈጸማቸዉ ታሪካዊ በደሎች ዋንኛዉ የሃገሪቱ የሉዓላዊነትና የህልውና ጋሻ የሆነውን የሃገር መከላከያ ሰራዊትን ለማዳከም መሞከሩ ነው፡፡
ሰራዊቱ የኢትዮጵያዊነት ልክ እና በሃገሩ ብሄራዊ ጥቅም የማይደራደር መሆኑን ጠንቅቆ ስለሚያውቅ በተለያዩ ስልቶች ሰራዊቱን ሲያዳክም ኖሯል፡፡
ቡድኑ የሃገር መከላከያ ሰራዊትን ያዳከመ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን የባህር በር ያሳጣ እና የኢትዮጵያ ባህር ኃይልን ያፈረሰ ነው፡፡
የሰሜን ዕዝን በጭካኔ የጨፈጨፈ ፤ ጽምዶን መስርቶ ከሻዕቢያና ግብጽ ጋር ግንባር ፈጥሮ ሃገሩን የወጋ ነው፡፡
ህገወጡ ህወሃት ኢትዮጵያ እንደ ሃገር ጸንታ የምትቆምባቸዉን ጠንካራ ተቋማት ካፈረስን ሃገሪቱን በቀላሉ ማዳከምና ለውጭ ወራሪ ሃይሎች አሳልፈን መስጠት እንችላለን የሚል እኩይ ፍላጎት ያለው ሃገር አፍራሽ ቡድን ነው፡፡
ዛሬ ላይ ግን በሃገራዊ ሪፎርሙ የዉስጥ ባንዳዎችን እና የዉጭ ታሪካዊ ጠላቶችን በአጭር ጊዜ ዉስጥ መመከት የሚችል ጀግና ሰራዊት ተገንብቷል፡፡
የተሰጠውን ተልዕኮ በአጭር ጊዜ ዉስጥ በመፈጸም አይበገሬነቱንና አስተማማኝነቱን እያስመሰከረ የሚገኘው ጀግናው የሃገር መከላከያ ሰራዊት ከሁሉም ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች የተውጣጣ ፣ የሀገሪቱን ታሪክ ፣ እሴቶችና የሀገር ፍቅር ተሸክሞ የቆመ ጠንካራ ሃይል ነዉ፡፡
ሰራዊቱ በህብረ ብሄራዊ አንድነት ጽኑ መሰረት ላይ ከመገንባቱም ባሻገር ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎችና ቴክኖሎጂዎችን የታጠቀ መሆኑ ደግሞ ግዳጁን በአጭር ጊዜ ውስጥ በላቀ ጀግንነት እንዲፈጽም ትልቅ አቅም ፈጥሮለታል፡፡
መከላከያዉ ከመላው ኢትዮጵያዊያን አብራክ የተገኘ ሲሆን በሃገሩ ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ጥቅም ላይ ከማንም ጋር የማይደራደር መሆኑንም ሰሞኑን እየፈጸመ በሚገኘዉ አኩሪ ድል በማስመስከር ላይ ይገኛል፡፡
የትናንቱን የጀግንነት ታሪክ የወረሰው ጀግናው የሃገር መከላከያ ሰራዊት በሰሜኑ የሃገሪቱ ክፍል ሰሞኑን ካስመዘገባቸዉ አኩሪ ድሎች ባሻገር ህዝቡ በየቦታው እያደረገለት ያለው አቀባበልና ድጋፍ ሰራዊቱ በህዝብ ዘንድ ያለዉን ተቀባይነትና እምነት የሚያረጋግጥ ነው፡፡
ከአድዋ ጀግኖች የተረከባትን ሃገር በጀግንነት እያገለገለ የሚገኘው ሰራዊቱ የተረከባትን ሃገር በጠንካራ ህብረ ብሄራዊ አንድነት ላይ ገንብቶ ለነገው ትውልድ ለማስረከብ በቆራጥና ጽኑ ሃገራዊ ወኔ በመታገል ላይ ይገኛል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ