AMN – ጥቅምት 3/2019 ዓ.ም

በሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ችግሮችን በመቅረፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ ፈጣን ለውጥ ማምጣት እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አሳሰቡ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የበጀት ዓመቱን የ1ኛ ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ማጠቃለያ ላይ ማብራሪያ የሰጡት ከንቲባዋ፣ በትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ጠንከር ያለ መመሪያ ሰጥተዋል።

ከንቲባዋ የትራንስፖርት ዘርፍ ሪፖርት «ምን ያህል ሰው ተጓጓዘ?» የሚለውን ብቻ ደምሮ አጠቃላይ መረጃ ማስቀመጥ ተገቢ እንዳልሆነ ገልጸው፤ «ሰው ተጓጉዟል፤ አዎ! ግን ስንት ሰዓት ቆይቶ ነው የተጓጓዘው? ምን ያህልስ ነው የጠበቀው? ምክንያቱም በዚሁ መንገድ ከልሄድን የምንለካበት ልኬት ስተት ይሆናል» ብለዋል።
ህዝቡ በአውቶብስ ማቆሚያዎች ለረጅም ሰዓታት የሚጠብቅበትን ጊዜ ማሳጠር እንደሚያስፈልግ አጽንኦት የሰጡት ከንቲባ አዳነች፤ የከተማዋ ነዋሪዎች በአውቶብስ መጓጓዝ ብቻ ሳይሆን በክብር መስተናገድን የሥራ አፈጻጸም ዋና መለኪያ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

አውቶብሶች በፍጥነት ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ ከማድረግ ባለፈ፣ የአውቶብስ አጠቃቀምና ከአሽከርካሪዎች ጀምሮ በዲሲፕሊን የማስተዳደር ሥራዎች ላይ ግልጽ ችግሮች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
በከተማ አስተዳደሩ በኩል በትራንስፖርት ዘርፍ በርካታ መሠረተ ልማቶች መገንባታቸውን እና አሁን ላይ ተጨማሪ 600 አውቶብሶች በግዥ ላይ መሆናቸውን ከንቲባ አዳነች ገልጸዋል።
ሙሉ በሙሉ ሰልፍን ማስቀረት ባይቻልም እንኳን አገልግሎቱን ፈጣንና ቀልጣፋ ማድረግ እንደሚገባ ከንቲባዋ ገለፀው፣ ያሉትን አውቶብሶች በተገቢው ስምሪት ላይ መሆናቸውን፣ በተገቢው ሰዓትና በክብር እያስተናገዱ መሆኑን መከታተልና ማስተካከል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በታደሰ ሽፈራው