የባህር በሩ እጀታ ተይዟል !

AMN – ጥቅምት 4/2019 ዓ.ም

ፈርዖኖቹ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ለማስተጓጎል ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም፡፡

አለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ጫናዎችንና የሀገርን ገጽታ የሚያጠለሹ የሚዲያ ዘመቻን ከማካሄድ ጀምሮ እንደ ጽምዶና ሻዕቢያ ያሉ ታጠቂ ኃይሎችን ቀጥረው ኢትዮጵያን እስከ መውጋት ደርሰዋል፡፡

የሦስትዮሽ ድርድርን ምክንያት አድርገው የከረረ የቃላት ጦርነት ፣ ዛቻና ማስፈራሪያ ቢጠቀሙም ሰሚ አላገኙም፡፡

ኢትዮጵያ በበኩሏ ግድቡ የሌሎች ሀገራትን የውሃ ተጠቃሚነት እንደማይጎዳ ፣ ይልቁንም ቀጣናውን በኃይል እንደሚያስተሳስር በተደጋጋሚ ስትገልጽ ቆይታለች፡፡

ኢትዮጵያ ፕሮጀክቱን አጠናቅቃ ቀጣናውን በኃይል ካስተሳሰረች በኋላም ቢሆን ፣ ግድቡ በታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ላይ ምንም አይነት ተጽእኖ አለማድረሱ የፈርዖኖቹን ሃሰተኛ ክስ እና ጩህት ይበልጥ ተቀባይነት አሳጥቶታል፡፡

ፈርዖኖቹ ኢትዮጵያን በተደጋጋሚ የሚከሱት በውሃ አቅርቦቱ ላይ የተፈጠረ ለውጥ ስላለ ሳይሆን የአባይን ወንዝ በብቸኝነት ለመጠቀም ካላቸው ስግብግብ ፍላጎት የመነጨ መሆኑንም ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ መድረኮች ጭምር አጋልጣለች፡፡

ኢትዮጵያን በተለያዩ ስልቶች ለማዳከም በርካታ ሴራዎችን ስትፈጽም ቆይታ አልሳካላት ያለው ግብጽ ፣ ኋላ ላይ በውክልና ጦርነት የጂኦፖለቲካ ከበባ ውስጥ ገብታለች፡፡

ይህ የግብፅ እብሪተኛ እርምጃ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ፍላጎት የሚጻረር እና ቀጣናውን ወደ ከፋ አለመረጋጋት የሚወስድ ነው፡፡

ሻዕቢያ እና ጽምዶ ሰሞኑን በኢትዮጵያ ላይ ይፋዊ ጦርነት ያወጁት ይህንኑ የፈርዖኖቹን የጂኦፖለቲካ ከበባ ለማሳካት ሲሆን ፤ የፈርዖኖቹ ድብቅ ሴራም በጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ጠንካራ እርምጃ ሙሉ በሙሉ እየከሸፈ ይገኛል፡፡

ግብጽ የሱዳን ግጭት ተዋናዮችን ከኋላ ሆና በመደገፍ በቀጣናው ላይ ተጨማሪ ተጽእኖ ለመፍጠር ያደረገችው እንቅስቃሴም በፍጹም አልተሳካም፡፡

ካይሮ የሞከረችው የጂኦ ፖለቲካ ከበባ የኢትዮጵያዊያንን አንድነት ፣ ህብረትና ጥንካሬ ይበልጥ ያጎላ ሲሆን ለታሪካዊ ጠላቶቿም ትልቅ ማስተማሪያ ሆኗል፡፡

ምንም አይነት የውጭ ጫና ፣ የድንበር ትንኮሳ እና የውክልና እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሃብቷ እንዳትጠቀም፤ እንዳትለማ እና እንዳትበለጽግ ሊያስቆማት አይችልም፡፡

የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ግብጽ ፍጹም አግባብነት ለሌለዉ ፖለቲካዊ ጥቅሟ ብላ የምስራቅ አፍሪካን ሰላም በመሸርሸር እና በማደፍረስ ላይ መሆኗን በመረዳት ላይ ይገኛል፡፡

ግብጽ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም አደናቅፋለሁ ብላ ለዘመናት ስትኳትን ብትኖርም ፤ ኢትዮጵያ ግን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ በአባይ ወንዝ የመጠቀም ፍላጎቷን እውን ከማድረግ አልፋ በህገወጥ መንገድ ያጣችውን የባህር በር ለመመለስ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡

የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ የባህር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት እየደገፈ ይገኛል፡፡

ይህም ፈርዖኖቹ ለረጅም ዘመናት ኢትዮጵያን ለማዳከም ያላቸውን ድብቅ ፍላጎት ሙሉ በሙሉ ያከሸፈ ሲሆን ለኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞም አዲስ ምዕራፍ በመክፈት ላይ ይገኛል፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review