AMN- ጥቅምት 7/2019 ዓ.ም

በኢትዮጵያ የሚገኙ የልዩ ልዩ ሀገራት ዓለም አቀፍ ወታደራዊ አታሼዎች የኢፌዴሪ ሀገር መከላከያ ሠራዊት የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር የሚያደርገውን ጥረት እና ያሳየውን ከፍተኛ ሰብዓዊነት እንደሚደግፉ ገለጹ።

ለተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ አታሼ አባላት በቢሾፍቱ አየር ኃይል ቤዝ በኢትዮጵያ ስላለው ነባራዊ ሁኔታ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል።
ወታደራዊ አታሼዎቹ በሰጡት አስተያየት፣ በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ በማኅበራዊ ሚዲያዎች እና በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ያልተረጋገጡና የተሳሳቱ መረጃዎች ሲሰራጩ መቆየታቸውን አውስተዋል።
የመከላከያ ሠራዊት ዓለም አቀፉን የዲፕሎማቲክ እና የወታደራዊ አታሼ ማኅበረሰብ በመጋበዝ የሰጠው ይፋዊ ገለጻ የነበሩ የመረጃ ክፍተቶችን በመድፈን፣ ትክክለኛውንና ወቅታዊውን ሁኔታ ለማወቅ እንደረዳቸው ገልጸዋል።

የእንግሊዝ፣ የአውስትራሊያ፣ የባንግላዴሽ፣ የኬንያ፣ የጋቦን፣ የደቡብ ሱዳንና የታንዛኒያ ወታደራዊ አታሼዎች በሰጡት አስተያየት፣ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ግዴታዋን በመወጣት የሀገሯን ሉዓላዊነት፣ የድንበር አንድነት እና የዜጎቿን ደኅንነት የማስከበር ሕጋዊና ተፈጥሯዊ መብት ያላት መሆኑን አረጋግጠዋል።
የባንግላዴሽ እና የታንዛኒያ ወታደራዊ አታሼዎች በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ዓለም አቀፍ የጦር ሕጎችን እና ሰብዓዊ መብቶችን ጠብቆ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ሠራዊቱ የንጹሐን ዜጎችን ሕይወት መጠበቅ እና ሕጋዊ ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ ብቻ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑን አድንቀዋል።
የኢትዮጵያ ሰላም እና መረጋጋት በቀጥታ ለጎረቤት ሀገራት እና ለመላው የአፍሪካ ቀንድ ሰላም ወሳኝ ነው ያሉት ደግሞ የኬንያ እና የደቡብ ሱዳን ተወካዮች ናቸው፡፡
ዓለም አቀፍ ወታደራዊ አታሼዎች የሀገር መከላከያ ሠራዊት የጀመረው የሰላም እና የፀጥታ ማስከበር ሥራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ዘላቂ መረጋጋትን እንደሚያመጣ ያላቸውን እምነት ገልጸው፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ኢትዮጵያ ለምታደርገው የሰላም ጥረት ከጎኗ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።