AMN – ጥቅምት 8/2019 ዓ.ም

ለሀገራዊ መግባባት የሚረዱ ምክረ ሃሳቦችን ለመተግበር መንግሥት ዝግጁነቱን በይፋ መግለጹ ለውጤታማነቱ መሰረት መሆኑን የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ገለጹ።
ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል የተካሄደው የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በስኬት መጠናቀቁ ይታወሳል።
ምክክሩ በሕዝቦች መካከል ሀገራዊ አንድነትንና ወንድማማችነትን በጽኑ መሠረት ላይ ለመገንባት የሚያስችል አዎንታዊ መንገድ አመላክቷል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ እንዳሉት፣ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ኢትዮጵያውያን በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድነት ተሰባስበው በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በሰፊው የመከሩበት ነው።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የተለያዩ አመለካከቶችና ልዩነቶች ቢኖሯቸውም ምክክር ለሀገሪቱ ዘላቂ እድገትና ሰላም እጅግ አስፈላጊ መሆኑ ላይ የጋራ አቋም መያዛቸውን አውስተዋል።
በዚህ ታሪካዊ የምክክር ሂደት ውስጥ 42 የሚሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች በንቃትና በባለቤትነት መሳተፋቸውንም ተናግረዋል።
የምክክር ሂደቱ የሁሉም ወገኖች ድምፅ የተሰማበት፣ አሳታፊነቱንና አካታችነቱን ያረጋገጠ ታሪካዊ ክስተት ሆኖ መመዝገቡን አስገንዝበዋል።
ሀገራዊ መግባባትን ለማስፈንና ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት የሚያስችሉ ልዩ ልዩ ምክረ ሀሳቦችን ለመተግበር መንግሥት ዝግጁነቱን ማስታወቁ ለውጤታማነቱ ትልቅ እርምጃ እንደሆነም ነው የተናገሩት።
የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በሂደቱ የምክረ ሀሳቦችን የትግበራ ሂደት ለመከታተል የሚያስችል አጠቃላይ ስትራቴጂያዊ ዕቅድ በማዘጋጀት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማቅረቡን ፕሮፌሰር መስፍን ገልጸዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።
የክትትልና ቁጥጥር ሥራው ስኬታማ ይሆን ዘንድ ምክር ቤቱ ከተለያዩ የመንግሥትና የሕዝብ ተቋማት ጋር በቅንጅትና ትብብር እንደሚሠራ አንስተዋል።