AMN- ጥቅምት 9/2019 ዓ.ም
ተግባራት በክላስተር በመፈፀማቸው የተገልጋይን እርካታ ማሳደግ አስችሎናል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ የማህበራዊ ክላስተር አባል ሴክተር መስሪያ ቤት አመራሮች ተናገሩ።
ተግባራትን በክላስተር አቅዶና አስተባብሮ መፈጸም መቻሉ የተበጣጠሱ አሰራሮችን በማስቀረት፣ ጊዜና ሀብትን በመቆጠብ እንዲሁም የተገልጋይን እርካታ ያሳደጉ ስኬታማ አፈጻጸሞችን ለማስመዘገብ አስችሏል።
የአዲስ አበባ ከተማ የቅንጅት ስራዎች የማህበራዊ ክላስተር የ2019 በጀት ዓመት የ1ኛ ሩብ ዓመት የእቅድ አፈጻጸሙን ገምግሟል።
ክላስተሩ ማህበራዊ አገልግሎቶች በተቀናጀ መልኩ እንዲሳለጡ፣ የላቀ ውጤታማነት እንዲሰፍን እንዲሁም ጠቃሚ ባህላዊ እሴቶች እንዲጎለብቱ በማድረግ ለከተማዋ ነዋሪዎች ደረጃቸውን የጠበቁ አገልግሎቶች እንዲሰጡ ለማስቻል በስሩ 10 መስሪያ ቤቶችን አቅፎ ወደ ተግባር ገብቷል።
የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ኃላፊና የክላስተሩ ሰብሳቢ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ አደረጃጀቱ ካለፈው በጀት ዓመት የተገኙ ልምዶችን እንደ መነሻ በመውሰድ የተጠቃለለ እቅድ በማዘጋጀት ወደ ተግባር መግባቱን ተናግረዋል።

በግምገማ መድረኩ ላይ የተሳተፉ የክላስተሩ አባል መስሪያ ቤት ኃላፊዎች በበኩላቸው፣ በሩብ ዓመቱ የተገልጋዩን ማህበረሰብ እርካታ ያሳደጉ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎቶችን መስጠት መቻሉን ገልጸዋል።
በሩብ ዓመቱ ለተገኙ ውጤቶች ስራዎችን በቅንጅት መስራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ጠቁመዋል።
ቅንጅቱ ጊዜንና ሀብትን በመቆጠብ ውጤታማ ስራዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ እውን ለማድረግ እንዳስቻላቸው የገለጹት የክላስተሩ ኃላፊዎች፣ በቀሪ ወራቶች በትኩረት ሊከናወኑ የሚገባቸውን አቅጣጫዎችም አስቀምጠዋል።
በታምሩ ደምሴ