ከስብራት ወደ ሉዓላዊ ከፍታ፦ በመደመር መንግሥት እሳቤ፣ የቀጣናው መልህቅ የሆነችው ኢትዮጵያ

You are currently viewing ከስብራት ወደ ሉዓላዊ ከፍታ፦ በመደመር መንግሥት እሳቤ፣ የቀጣናው መልህቅ የሆነችው ኢትዮጵያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቆይታቸው፣ ኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች ያላትን ታላቅ አቅም፣ ፈተናዎችን ተሻግራ ያስመዘገበቻቸውን አመርቂ ድሎችና ራስን የመቻል ሉዓላዊ ጉዞ አስምረውበታል።

ዓለም በጂኦፖለቲካዊ ውጥረት፣ በንግድ መስመሮች መታወክና በኢኮኖሚ መንገራገጭ በምትናጥበት ዘመን፣ ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተገበረቻቸው መሠረታዊ የሪፎርም ሥራዎች ጫናዎችን የመቋቋም ብቃቷን በተግባር አረጋግጣለች።

የመደመር መንግሥት እሳቤ ዋነኛ ፍልስፍናና ሚና ሀገራዊ ጸጋዎቻችንን አቀናጅቶ፣ ካለን የተፈጥሮና የሰው ኃይል ዕምቅ አቅም ተነስቶ የማድረግ ብቃትን መገንባት፣ ያንንም ወደ ጽኑ ሀገራዊ ኃይልና ሉዓላዊ ልዕልና ማሸጋገር ነው።

መንግሥት ራሱን እንደ ሀገር ባለአደራ በመቁጠር፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሻገር ጠንካራ ተቋምና የሥልጣኔ መሠረት ለመጣል እየሠራ ይገኛል። በዚህ የመደመር መንግሥት መሪነት የተመዘገቡት ተጨባጭ ውጤቶችም ሀገራችን ወደ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ መግባቷን ይመሰክራሉ።

በኢኮኖሚው መስክ፣ ኢትዮጵያ 210 ቢሊየን ዶላር አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት በማስመዝገብ በምሥራቅ አፍሪካ አንደኛዋ፣ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ደግሞ ሦስተኛዋ ግዙፍ ኢኮኖሚ መሆን ችላለች።

በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ የኢንዱስትሪው ዘርፍ 31.8 በመቶ ድርሻ በመያዝ ከግብርናው የላቀ ምዕራፍ ላይ መድረሱ፣ ሀገራችን ወደ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር መግባቷን ያበስራል።

የውጭ ምንዛሬ ክምችታችን ከ20 እጥፍ በላይ ማደጉ፣ በአንድ ሩብ ዓመት ብቻ የቀድሞውን የአንድ ዓመት የወጪ ንግድ የሚያክል 3.1 ቢሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱ፣ እንዲሁም 6 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ የውጭ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት መቻሉ ኢትዮጵያ ከጥገኝነት ተላቃ በራሷ እግር መቆም መጀመሯን የሚያረጋግጡ ሕያው ማሳያዎች ናቸው።

ራስን የመቻልና የ«እንችላለን» መንፈስ በግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችና በተቋማት ግንባታም በደማቁ ተጽፏል።

የኢትዮጵያ ባቡር ኮርፖሬሽን ከውጭ አስተዳደር ወጥቶ በሀገር ልጆች ብቃት በመመራት ዓመታዊ ትርፉን ከ3.4 ቢሊየን ብር ወደ 43 ቢሊየን ብር ማሳደጉ፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ አጠቃላይ ሀብቱን ሦስት እጥፍ በማሳደግ 9 ትሪሊየን ብር ማድረሱ የሀብት ብክነትን ወደ ልማት የቀየረ ታላቅ ስኬት ነው።

ከታላቁ የሕዳሴ ግድብ ባሻገር የኮይሻ ግድብ፣ የጎዴ ማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የጋዝ ልማትና የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታዎች በተግባር መሬት ላይ መውረዳቸው፤ እንዲሁም በከተሞች የኮሪደር ልማትና በአረንጓዴ አሻራ የተመዘገበው ውጤት ኢትዮጵያን በአፍሪካ ብሎም በዓለም አቀፍ መድረክ የልማት ተምሳሌትና የታላላቅ ጉባኤዎች መናኸሪያ አድርጓታል።

በፖለቲካዊ ባህላችንና በሀገራዊ መሻገር ረገድ፣ የመደመር መንግሥት የቂምና የመጠፋፋት ታሪክን በመስበር የምክክርና የይቅርታን መንገድ መርጧል። ላለፉት አራት ዓመታት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ያሳተፈው ሀገራዊ ምክክር፣ የቀደመውን «የመቅደድና የማፍረስ» የፖለቲካ ልምምድ ቀይሮ፣ ጠቃሚውን በማቆየትና ክፍተቶችን በሰከነ ውይይት በማረም ወደ ዘላቂ መግባባት የምንሻገርበትን ታሪካዊ ድልድይ ዘርግቷል።

አሸንፎ ሰላምን በመፈራረም፣ በይቅርታና በትዕግሥት የውስጥ ሽኩቻዎችን ለመፍታት የተደረገው ጥረት፣ ሀገራችንን ከውስጥ አጥፊ አባዜዎች (Auto-immune disease) አላቅቆ ወደ ጽኑ ሀገራዊ አንድነት ለማሻገር ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል።

በሉዓላዊነትና በቀጠናዊ ዲፕሎማሲ ረገድ ደግሞ፣ ኢትዮጵያ «ከምንጭ የተጠጋ ዋርካ ሁሌ ይፈካል» በሚል መርሕ ለጎረቤቶቿ ሰላምና የጋራ ልማት ቅድሚያ የምትሰጥ የቀጠናው መልህቅና ታላቅ ወንድም ናት።

በብሔራዊ ጥቅሞቿና በሉዓላዊነቷ ላይ ግን ፈጽሞ የማትደራደር፣ ማንንም የማትወር ነገር ግን የሚነካትን የማትታገሥ ጽኑ ሀገር ናት። ራሱን በቴክኖሎጂ፣ በሰው ኃይልና በራስ አቅም ምርት የገነባው የሀገር መከላከያ ሠራዊታችን ሀገርን የመጠበቅና የቀጠናውን ሰላም የማስከበር አስተማማኝ ቁመና ላይ ይገኛል።

የቀይ ባህር ተደራሽነትን ጨምሮ የታሪክና የጂኦግራፊ ሀቃችንን በሰጥቶ መቀበልና በሰላማዊ ንግግር ለማረጋገጥ የተጀመረው ስትራቴጂካዊ መነቃቃትም ኢትዮጵያን ከተዘጋ ቀጠና አውጥቶ ለጋራ ብልጽግና መሠረት የሚጥል ነው።

በእርግጥም የኢትዮጵያ ጉዞ ከስብራት ወደ መጠገን፣ ከጥገኝነት ራስን ወደ መቻል፣ ከአለመቻል ወደ መቻል፣ ከአለማድረግ ወደ ማድረግ፣ ከድህነትና ረሃብ ምሳሌነት ወደ አምራችነትና ላኪነት፣ ወደ ብልጽግናና ልማት ተምሳሌትነት፣ እንዲሁም ከኋሊት ጉዞ ወደ ፈጣን የእድገትና የግስጋሴ ጉዞ የተደረገ ታላቅ ታሪካዊ ሽግግር ነው። ኢትዮጵያ የአንድ መንግሥት የግል ሀብት ሳትሆን የሁላችንም የጋራ ቤትና ታላቅ አደራ ናት።

ስለሆነም፣ መላው ኢትዮጵያውያን ዜጎች በመደመር መንግሥት መሪነት የምትሄደውን የታላቋን ኢትዮጵያ የመገንባት ጉዞ በትብብር፣ በአብሮነት፣ በጋራ እጅ ለእጅ በመያያዝና በሕብረ ብሔራዊ አንድነት ከግብ ለማድረስ ሁሉም በየተሰማራበት መስክ እንዲነሳ ጥሪ እናቀርባለን።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review