ኢትዮጵያ በቬይትናም እየተካሄደ ባለው ጉባዔ የስርዓተ ምግብ ተሞክሮዋን አጋራች
AMN – ሚያዝያ 9/2017
ኢትዮጵያ በፒ4ጂ ቬይትናም ጉባኤ ላይ የስርዓተ ምግብ ስራዋን አስመለክቶ ልምዷን አካፍላለች።
ጉባኤው “ዘላቂ እና ህዝብን ማዕከል ያደረገ አረንጓዴ ሽግግር” በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ይገኛል።
ከአረንጓዴ አብዮት ጋር የተጣጣመ ዘላቂ የስርዓተ-ምግብ ሽግግር የተመለከተ የሚኒስትሮች መድረክም ተካሄዷል።
ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ የስርዓተ-ምግብና ኒውትሪሽን ፍኖተ-ካርታ አዘጋጅታ እየተገበረች እንደምትገኝ በመድረኩ ላይ ቀርቧል።
በተለይም ሀገር በቀል የአረንጓዴ አሻራ፣ የስንዴ ልማት እና የሌማት ትሩፋት ፕሮግራሞች ዘላቂ የምግብ ስርዓትና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ግብርናን ለማረጋገጥ መሰረት እየጣሉ መሆናቸው ተነስቷል።
የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ከመድረኩ ጎን ለጎን ከቬይትናም የተፈጥሮ ሀብት እና ከባቢ አየር ሚኒስትር ዱ ዱች ዱይ (Do Duc Duy) ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱም ሁለቱ ሀገራት በግብርናው ዘርፍ በተለይም በሩዝ ልማት ላይ በትብብር ለመስራት የጋራ መግባባት ላይ መድረሳቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።