የፕሪቶሪያ ስምምንት ለትግራይ ህዝብ እፎይታ አምጥቷል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 42ኛ መደበኛ ስብሰባውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት እያካሔደ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በመስጠት ላይ ናቸው።
የትግራይ ክልልን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያም የፕሪቶሪያ ስምምንት የትግራይ ህዝብ ልጆቹን በየቀኑ ከማጣት ታድጓል ነው ያሉት።
ስምምነቱ ለኢትዮጵያ ህዝብና ለሌሎች ሀገራት ደግሞ መንግስት ሰላም ይሻላል ብሎ ለተዋጉት ኃይሎች እድል ይሰጣል የሚል አዲስ ባህል መፍጠሩን ጠቁመዋል።
በክልሉ አገልግሎትን በሚመለከት ቴሌኮም፣ ባንኮች፣ አየር መንገድና ሌሎችም አገልግሎቶች ሙሉ ለሙሉ ጀምረዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የተፈናቀሉ ሰዎችን በሚመለከት ራያ መቶ በመቶ ጸለምትም ተመልሰዋል።
ቀሪ ወልቃይት ያልተመለሱ አሉ፤ መንግስት ያልተመለሱ ተፋናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ የጸና አቋም ነው ያለው ብለዋል።
የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ ማቋቋምና ወደ ማህበረሰቡ መቀላቀልም በፍጥነት መፈጸም እንዳለበት ገልጸው፥ይህ ጥቅሙ ለክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጭምር ነው ያሉት።
የፌደራል መንግስት ትግራይ ክልል ውስጥ ያሉ ጉዳዮችን በሰላም የመፍታት ፅኑ አቋሙን በተደጋጋሚ ማሳየቱን ገልጸው፤የትግራይ ህዝብ ጦርነት ፈጽሞ አይፈልግም ሲሉ አብራርተዋል።
ሆኖም የዓለምን ሁኔታና የዘመኑን ውጊያ ባለመገንዘብ፣ መንግስት በተለያዩ ችግሮች ተወሯል፤የሚያግዙን ሀገራት አሉ በሚል የተሳሳተ ስሌት ጊዜው አሁን ነው በሚል ውጊያ ለመክፈት የሚፈልጉ መኖራቸውን ተናግረዋል።
ይህ የተሳሳተ አካሄድ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ትግራይ የሚያስፈልገው ሰላም፣ ችገሮችን በውይይት በንግግር መፍታት ነው ብለዋል።
የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ ወደ ጦርነት እንዳይገባ አሁኑኑ የሰላም ሚናችሁን ተወጡ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
መንግስት አንድም ጥይት የመተኮስ ፍላጎት እንደሌለው በመጠቆም፥ሀገር ማልመት ነው ፍላጎታችን፤ ሁሉም ህዝብ ማወቅ ያለበት ጦርነት አያስፈልግም ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ትግራይ ክልልን ጨምሮ ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት ሁሉም የበኩሉን ሚና ማበርከት አስፈላጊ ስለመሆኑ ገልጸዋል።