AMN- ሐምሌ 19/2018 ዓ.ም
መከላከያ ሰራዊት ዘመኑን የዋጁ ቴክኖሎጅዎችን በመታጠቅ የሀገርን ዳር ድንበር እና የዜጎችን ክብር በተጠንቀቅ የሚጠብቅ የኢትዮጵያ ጋሻ እና መከታ ነው ሲሉ የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሀመድ ተናገሩ፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ የኢንጂነሪንግ እና ነርሲንግ የላቀ ላብራቶሪ አስመርቋል፡፡

ይህ ማዕከል የረቀቁ ቴክኖሎጅዎችን ከመትከል ባለፈ እውቀትን ወደ ሙያዊ ብቃት የሚያልቅ ምርምርን ወደ ፈጠራ የሚለውጥ እና ተግባራዊ መፍትሄዎችን እዉን የሚያደርግ መሆኑን የመከላከያ ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከሀገራት ጋር ዘመናትን የተሻገረ በጋራ ተጠቃሚነት እና በስትራቴጅካዊ አጋርነት የተቃኘ ግንኙነት አላት ያሉት ሚኒስትሯ፣ ይህ ማዕከልም በኢትዮጵያ እና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ትብብር እዉን የሆነ ነው ብለዋል፡፡
ማዕከሉ የመከላከያ ሰራዊትን ሁለንተናዊ የመዘመን ጉዞ የሚያፋጥን የቴክኖሎጂ እና የምርምር መሰረትን በማጎልበት ሀገራዊ ደህንነትን በፅኑ መሰረት ላይ የሚያቆም መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ የኢንጂነሪንግ እና ነርሲንግ አድቫንስድ ላብራቶሪ በ11 ሺህ ካሬ ሜትር መሬት ላይ ያረፈው ይህ ማዕከል፣ ሁለት የኤ አይ ላብራቶሪዎች፣ ሁለት የሳይበር ላብራቶሪዎች እና ሁለት የ3ዲ ላብራቶሪዎች በውስጡ እንደሚገኙ ተመላክቷል።
ማዕከሉ አምስት ዘመናዊ ስማርት ክፍሎች እና የምርምር ቦታዎች የተዘጋጁለት ሲሆን፣ የሶላር ኃይል ሥርዓት እና ዘመናዊ መሳሪያዎችም ተገጥመውለታል፡፡
በተመስገን ይመር