የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 42ኛ መደበኛ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በተገኙበት ተካሂዷል።
በግብርናው ዘርፍ ሜካናይዜሽንን የሚያስፋፉ በሺህ የሚቆጠሩ ትራክተሮችን በማስገባትና የመስኖ ልማትን በማስፋፋት ምርታማነትን ማሳደግ መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አስታወቁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግብርናውን ሜካናይዝድ ለማድረግና ምርትን ለማሳደግ በሺዎች የሚቆጠሩ ትራክተሮችና ፓምፖች ጥቅም ላይ መዋላቸውንና የግብርና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችም በእያንዳንዱ አርሶ አደር ማሳ ላይ ቀን ከሌት እየተጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በግብርናው ዘርፍ አዳዲስ የስራ ልምምድ መኖሩን ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሞቃታማ አካባቢዎች ማታ ጭምር እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡
ኖራን በማምረት ከ50ሺህ ሄክታር በላይ አሲዳማ መሬት ታክሞ ወደ እርሻ መግባቱን ገልፀው መሬትን ደጋግሞ የማረስና በአመት ሁለቴ ሶስቴ የማምረት ልምምድ ማደጉን በተለይ የበጋ መስኖ መጀመሩ ከፍተኛ እመርታ አምጥቷል ብለዋል፡፡
በሌማት ትሩፋት በዶሮ ልማት፣ የእንቁላልና የወተት ምርት ያደገበት፣ በሰው ሰራሽ ማዳቀል ዘዴ ምርታማነትን በመጨመር የወተት ፍጆታ በግለሰብ 66 ሊትር የነበረው ወደ 80 ሊትር ማደጉንም መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በማር እና በአሳ የታዩ ከፍተኛ ለውጦች እንደ መልካም ጅማሮ የሚወሰዱና ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን መተካት መቻሉን በመጥቀስ ይህ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና በብዙ ዘርፍ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል አውስተዋል፡፡
በቡና፣ በሻይና በሩዝ ልማት ላይም ለውጥ መኖሩን ጠቅሰው ግብርናው ትኩረት የተሰጠውና ትልቅ ውጤት ያመጣ እንዲሁም ለአጠቃላይ እድገታችን ትልቅ ድርሻ ያለው ነው ብለዋል፡፡