AMN – ሐምሌ 19/2018 ዓ.ም

በአየር ንብረት ለውጥ ስጋት ላይ የሚገኙ ከተሞች ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ፈታኝ ጉዞ እያደረጉ በሚገኙበት በዚህ ዘመን፣ አዲስ አበባ የሥነ-ምህዳር እና የኮሪደር ልማትን በማዋሃድ ለኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ተመራጭ መዳረሻ እየሆነች ትገኛለች።
ከተማዋን ለአየር ንብረት ለውጥ የማትበገር፣ ውብ እና ለነዋሪዎቿ ተስማሚ ለማድረግ የተጀመረው የ“አረንጓዴ አሻራ” መርሐ-ግብር ከኮሪደር ልማቱ ጋር ተዳምሮ አዲስ መልክ አላብሷታል።

“ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ ቃል የተጀመረው የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር፣ በታቀደለት ፍጥነትና በከፍተኛ ሕዝባዊ ተሳትፎ እየተከናወነ ይገኛል። በመዲናዋ ዘንድሮ 6 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ፣ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ ከአራት ሚሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል።
ባለፉት ሰባት ዓመታት በመዲናዋ 90 ሚሊዮን ችግኞች በመተከላቸው፣ ዝቅተኛ የነበረው የከተማዋ የአረንጓዴ ሽፋን ከ8 በመቶ ወደ 24 በመቶ ከፍ ማለት ችሏል። በዚህም የተራቆቱ አካባቢዎች አረንጓዴ ለብሰዋል፤ የነጠፉ ወንዞችም ማንሰራራት ጀምረዋል።

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ከአካባቢ ጥበቃ ባለፈ ለምግብ ዋስትና ትልቅ ትኩረት የሰጠ ሲሆን፣ በሂደቱም የኢኮኖሚ ፋይዳ ያላቸው ችግኞች፣ የከተማዋን ውበት የሚያጎሉ ጌጣጌጥና የጥላ ዛፎች በስፋት እየተተከሉ ይገኛሉ።
የከተማዋ አስተዳደር አዲስ አበባን ወደ ሥነ-ምህዳራዊ ዘመናዊ ከተማ ለመቀየር የሚያከናውናቸው ተግባራት ከኮሪደር ልማት ጋር ተዳምረው፣ ከተማዋን ለኢንቨስትመንት እና ለቱሪዝም ተመራጭ እያደረጓት ነው።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር ላይ እንደገለጹት፤ “የምንተክለው ተስፋን፣ ልማትን፣ ልምላሜን፣ ጥላን፣ ምግባችንን ብሎም ብልፅግናን ለትውልድ ለማውረስ ነው” ብለዋል።
ከተማዋን ውብ፣ ጽዱ እና ለኑሮ ምቹ ለማድረግ ሕዝቡን በማሳተፍ የተጀመረው ይህ የትውልድ አሻራ መርሐ-ግብር ዘንድሮም ተጠናክሮ ቀጥሏል።
በበረከት ጌታቸው
See less